ጀግናው!/ THE HERO!

አንበሳው!

ጀግናው

ሰው ጀግና ሊባል የሚገባው ለህልውናው አደገኛ እና አስጊ የሆነው አውሬ ሲያስወግድ፣ በብዙ ሰዎች ከባድ ተብሎ የተተወዉን ችግር ሲፈታ ወይም ለሰው ልጅ ጠቃሚ የሚሆን ቁምነገር ሲሰራ ነው። ጀግና የሚለውን ስያሜ የምንጠቀመው በተወሰነ ቦታ እና ጊዜ ውስጥ በማህበረሰብ ውስጥ የተለየ ወይም ማንም ሊያደርገው ያልቻለውን ከባድ ድርጊት እና ማንም ለወጣው ያልተቻለውን ፈተና በብቃት ሲወጣው ነው። ይህ ስያሜ በብዙ ማሀበረሰቦች (ሀገራት) እንደ ሽልማት የሚያገለግልና ለድል አድራጊዎች ብቻ የሚሰጥ ነው።
በድሮ ጊዜ በአንድ ህብረተሰብ ላይ ከሚከሰቱና ፈተና ከሚሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ሰውን ለማጥቃት ከዱር ወደ መንደሮች የሚገቡት አውሬዎች ከፍተኛ አደጋ ይፈጥራሉ። ከዚህም የተነሳ አውሬውን ገድሎ ሰዎቹን ከጭንቀት የሚገላግል ማንኛውም ሰው እንደ ማህበረሰቡ ጀግና ይቆጠራል፤ የአውሬውንም ቆዳ በመግፈፍ ይለብሰዋል። ሰዎች ከአውሬው ተገፈፈውን ቆዳ ሲመለከቱ የአውሬውን አደገኛነት ሲያስታውሳቸው ቆዳውን ገፍፎ የለበሰውን ሲያዩ ደግሞ ምንያህል ጠንካራ እና ጀግና እንደሆነ ያስተውላሉ። በዚህም ምክንያት በማህበረሰቡ ውስጥ ምርጥ የሆኑ ሽልማቶች ይበረከቱለታል፤ እንደ አስፈላጊነቱም ቆንጆ ኮረዳ ይታጭለታል።

ሰው ክቡር የሆነ ፍጡር መሆኑን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ማለትም የሰውን “አምላካዊ አሻራነት” በሚያምኑ ሀገራት በሰፊው የሚታመን ሃቅ ነው። ነገር ግን አለም ከተፈጠረች ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት በተቃራኒው የሰውን ክቡርነት ጥያቄ ውስጥ የሚከትቱ አሰቃቂ የሆኑ ግድያዎች ተከናውነዋል፤ በዚህ አይነት የታሪክ አጋጣሚ ጀግና ተብለው የተጠሩ ሰዎች ብዙዎች ናቸው። በእርግጥ የተገደለው ሰው ከአውሬ አልፎ ‘ጭራቅ’ የሚል ምናባዊ ስም የወጣለት ጨካኝ ወይም ጨቋኝ ሊሆን ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን ምንም እንኳን ይህ ተገዳይ ከፍተኛ ጥፋት በማህበረሰብ፣ በሀገር ላይ ቢያስከትልም ቅሉ፥ ቅን ፍርድ ግን ይገባዋል።

፨ ኧረ! ወራጅ አለ! ፤ ምንድን ነው የምትለው? ኢትዮጵያ እኮ የጀግኖች ሀገር ናት፤ የጀገኖች ሀገር የተባለችውም ለህልውናዋ፣ ዳር ድንበሯን ለማስከበር፣ ከወራሪ ሀይሎች በጠበቋት ልጆችዋ ነው። ታዲያ ምንድነው የምትለው?
ቅን ፍርድ ምን ማለት ነው? ቅን ፍርድ ማለት አንድ ሰው ወይም ማህበር (ለክፋት በህቡዕ የተደራጀ) ላደረጋቸው ነገሮች፣ ለተናገራቸውና ላቀዳቸው ሀሳቦች ተመጣጣኝ የሆነ፤ ከማንኛውም ግለሰባዊ መሻት እና ተጽዕኖ ነጻ የሆነ ብይን የሚሰጥበት ትክክለኛው (ideal) የፍርድ አይነት ነው።

ሰው በተፈጥሮው ያለ ስርዓት መኖር የማይችል፥ ኑሮው ሙሉ በሙሉ በስረዓት የተሞላ ፍጥረት ነው። በአንድ ቤት ውስጥ ስርዓት የሚያስከብር አባወራ (እማወራ) እንደሚያስፈልግ ሁሉ በአንድ ሀገር ደግሞ በመሪነት የተሾመ መሪ ያስፈልጋል። በአለማችን ብዙ ነገስታት እና ሀያላን አልፈዋል፤ አሁንም አለምን የሚያስተዳድሩ መልካም እና ክፉ ነገስታት ይገኛሉ። ዋናው ጥያቄ ግን እነዚህን መሪዎች ማን ሾማቸው? እንዴት ስልጣን ያዙ? የሚለው ይሆናል።

በሀገራችን ላለፉት መቶ አመታት አምስት ያህል መንግስታት/ነገስታት/፥ አፄ ምኒሊክ ፪ኛ፣ ልጅ ኢያሱ፣ ንግስት ዘውዲቱ፣ አፄ ኅይለሥላሴ፣ ሻለቃ መንግስቱ እና መለስ ዜናዊ፥ ብቻ ያለፉ ሲሆን ይህ ቁጥር ከሌሎች ማለትም ከሰለጠኑት የምዕራባውያን ሀገራት አንፃር ሲታይ እጅጉን የተለየ ቁጥር እናያለን። ያለፉት መንግስታት ቁጥር ብቻ ሳይሆን ስልጣን የተሸጋገረበትን መንገድ ስናይ ብዙዎቹ የስልጣን ሽግግሮች በደም የተጨማለቁ እና የብዙዎችን ህይወት በቀጠፉ ረብሻዎች እና ግርግሮች የተሞሉ ነበሩ።

//////////ይቀጥላል////////

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.