ይድረስ ለታጋይ/ተመራጭ/ እከሌ

ጀግና ማነው?

ሰው ጀግና ሊባል የሚገባው ለህልውናው አደገኛ እና አስጊ የሆነው አውሬ ሲያስወግድ፣ በብዙ ሰዎች ከባድ ተብሎ የተተወዉን ችግር ሲፈታ ወይም ለሰው ልጅ ጠቃሚ የሚሆን ቁምነገር ሲሰራ ነው። ጀግና የሚለውን ስያሜ የምንጠቀመው በተወሰነ ቦታ እና ጊዜ ውስጥ በማህበረሰብ ውስጥ የተለየ ወይም ማንም ሊያደርገው ያልቻለውን ከባድ ድርጊት እና ማንም ለወጣው ያልተቻለውን ፈተና በብቃት ሲወጣው ነው። ይህ ስያሜ በብዙ ማሀበረሰቦች (ሀገራት) እንደ ሽልማት የሚያገለግልና ለድል አድራጊዎች ብቻ የሚሰጥ ነው።

በድሮ ጊዜ በአንድ ህብረተሰብ ላይ ከሚከሰቱና ፈተና ከሚሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ሰውን ለማጥቃት ከዱር ወደ መንደሮች የሚገቡት አውሬዎች ከፍተኛ አደጋ ይፈጥራሉ። ከዚህም የተነሳ አውሬውን ገድሎ ሰዎቹን ከጭንቀት የሚገላግል ማንኛውም ሰው እንደ ማህበረሰቡ ጀግና ይቆጠራል፤ የአውሬውንም ቆዳ በመግፈፍ ይለብሰዋል። ሰዎች ከአውሬው ተገፈፈውን ቆዳ ሲመለከቱ የአውሬውን አደገኛነት ሲያስታውሳቸው ቆዳውን ገፍፎ የለበሰውን ሲያዩ ደግሞ ምንያህል ጠንካራ እና ጀግና እንደሆነ ያስተውላሉ። በዚህም ምክንያት በማህበረሰቡ ውስጥ ምርጥ የሆኑ ሽልማቶች ይበረከቱለታል፤ እንደ አስፈላጊነቱም ቆንጆ ኮረዳ ይታጭለታል።

ሰው ክቡር የሆነ ፍጡር መሆኑን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ማለትም የሰውን “አምላካዊ አሻራነት” በሚያምኑ ሀገራት በሰፊው የሚታመን ሃቅ ነው። ነገር ግን አለም ከተፈጠረች ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት በተቃራኒው የሰውን ክቡርነት ጥያቄ ውስጥ የሚከትቱ አሰቃቂ የሆኑ ግድያዎች ተከናውነዋል፤ በዚህ አይነት የታሪክ አጋጣሚ ጀግና ተብለው የተጠሩ ሰዎች ብዙዎች ናቸው። በእርግጥ የተገደለው ሰው ከአውሬ አልፎ ‘ጭራቅ’ የሚል ምናባዊ ስም የወጣለት ጨካኝ ወይም ጨቋኝ ሊሆን ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን ምንም እንኳን ይህ ተገዳይ ከፍተኛ ጥፋት በማህበረሰብ፣ በሀገር ላይ ቢያስከትልም ቅሉ፥ ቅን ፍርድ ግን ይገባዋል።

ኧረ ወራጅ አለ! ምንድን ነው የምትለው? ኢትዮጵያ እኮ የጀግኖች ሀገር ናት፤ የጀግኖች ሀገር የተባለችውም ለህልውናዋ፣ ዳር ድንበሯን ለማስከበር፣ ከወራሪ ሀይሎች በጠበቋት ልጆችዋ ነው። ታዲያ ምንድነው የምትለው?

ቅን ፍርድ ምን ማለት ነው?

ቅን ፍርድ ማለት አንድ ሰው ወይም ማህበር (ለክፋት በህቡዕ የተደራጀ) ላደረጋቸው ነገሮች፣ ለተናገራቸውና ላቀዳቸው ሀሳቦች ተመጣጣኝ የሆነ፤ ከማንኛውም ግለሰባዊ ወይም ቡድናዊ መሻት እና ተጽዕኖ ነጻ የሆነ ብይን የሚሰጥበት ትክክለኛው (ideal) የፍርድ አይነት ነው።

ሰው በተፈጥሮው ያለ ስርዓት መኖር የማይችል፥ ኑሮው ሙሉ በሙሉ በስረዓት የተሞላ ፍጥረት ነው። በአንድ ቤት ውስጥ ስርዓት የሚያስከብር አባወራ (እማወራ) እንደሚያስፈልግ ሁሉ በአንድ ሀገር ደግሞ በመሪነት የተሾመ መሪ ያስፈልጋል። በአለማችን ብዙ ነገስታት እና ሀያላን አልፈዋል፤ አሁንም አለምን የሚያስተዳድሩ መልካም እና ክፉ ነገስታት ይገኛሉ። ዋናው ጥያቄ ግን እነዚህን መሪዎች ማን ሾማቸው? እንዴት ስልጣን ያዙ? የሚለው ይሆናል።

አምባገነናዊ ስርዓቶች በኢትዮጵያ

በሀገራችን ላለፉት መቶ አመታት አምስት ያህል መንግስታት/ነገስታት/፥ አፄ ምኒሊክ ፪ኛ፣ ልጅ ኢያሱ፣ ንግስት ዘውዲቱ፣ አፄ ኅይለሥላሴ፣ ሻለቃ መንግስቱ እና መለስ ዜናዊ፥ ብቻ ያለፉ ሲሆን ይህ ቁጥር ከሌሎች ማለትም ከሰለጠኑት የምዕራባውያን ሀገራት አንፃር ሲታይ እጅጉን የተለየ ቁጥር እናያለን። ያለፉት መንግስታት ቁጥር ብቻ ሳይሆን ስልጣን የተሸጋገረበትን መንገድ ስናይ ብዙዎቹ የስልጣን ሽግግሮች በደም የተጨማለቁ እና የብዙዎችን ህይወት በቀጠፉ ረብሻዎች እና ግርግሮች የተሞሉ ነበሩ።

ከአጼ ኀይለ ሥላሴ ከንግስና መሻር አንስቶ ያለውን የስልጣን ሽግግር እንኳን ብንመለከት በብዙዎች ደም መፍሰስ የተመሰረተ ነው። ደርግ በተማሬዎች የተጀመረውን አብዮት ከዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ወደ ፖለቲካዊ ፍልስፍና ምርጫ በማላተም የዘመኑን ጥያቄ በጠመንጃ ሲመልስ እና ሀገሪቱን በዘመን የማትረሳውን አስከፊ ታሪክ ጽፎ አልፏል። በተጨማሪም የብዙ ሰዎችን እልቂት ያስከተለውን የረሀብ፣ የእርስ በርስ ጦርነቶችን እና ከፍተኛ የሆነ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዝቅጠት ውስጥ አስገብቷታል።

የደርግ አዛዝ ያለተመቻቸው የትግራይ እና የኤርትራ ወጣት ታጋዮች ወደ ትጥቅ ትግል ወስጥ በመግባት በታላቅ መሰረት ላይ ተጥሎ የነበረውን የደርግን ወታደራዊ መንግስት ለመደምሰ እና የኤርትራን መገንጠል ብሎም የአገዛዝ ስርኣት ቅያሬን አስከትሏል። በኤርትራ መገንጠል የተደሰተው የትግራይ ነጻ አውጭ (ወያኔ) ወዲያው ወደ ሀገራዊ ነጻ አውጪነት የፖለቲካ ጨዋታ ጀመረ።

ማንም ነጻ ያውጣ ማንም፡ በጦር አድማ የሚፈሰው ውኃ ሳይሆን የሰው ልጅ ክቡር ደም ነው፤ ለዚያዉም የወንድሞቻችን ደም። የሚያሳዝነው ግን፡ ነጻ አውጭነት ከሚሰጠው ክብር፣ ከጀግንነት ማዕረግ ወይም ሌላ ከህዝብ እውቅና ባለፈ ሌላ ቦታ በመፈለግ ያለፈውን እና የተገረሰሰውን ስርኣት በሚመልስ መልኩ ከህዝቦች እኩልነት ጥያቄ ወደ ክፍፍል አገዛዝ፣ ከፍርድ ጥያቄ ወደ ፍትህ ጉድለት፣ ከሰላም ጥያቄ ወደ እርስ በርስ የማናቆር ቅኝ አገዛዛዊ ሰርዓት በመመለስ ህዝብ በፍርሀት እና ጭንቀት እንዲሞላ እያደረገ ይገኛል።

ይድረስ ለታጋይ እከሌ፡-

ይህችን ፅሁፍ ታነባታለህ ለማለት ይከብደኛል ያው ቢያንስ ከልማታዊ ስራዎችህ የተረፈ ጊዜ ካገኘህ ብዬ በማሰብ ነው የፃፍኳት። እውነቴን ነው ምልህ ደርግን ለመደምሰስ ያደረከውን ትግል አደንቃለሁ፤ ያውም በወታደራዊ አቅም ጠንካራ የነበረውን አስፈሪውን ጦር። እኔ ግን የሚያሳዝነኝ፥ የነፃ አውጪው ወታደር ከህዝብ የወጣ የሀገር ልጅ እደሆነ ስትነግረኝ በጣም አዘንኩኝ እጅጉንም መሪር ሃዘን ውስጥ ገባሁ። አንዴ ብቻ ስማኝ!ለ23 ዓመታት የደሰኮርከው ጀግንነት የገዛ ወንድምህን እና ወገንህን ደም በማፍሰስ እንደሆነ ባለማገናዘብህ ብታፍር ደስታዬ ነው።

ምን??? በለኛ!
እሺ! ለምን መሰለህ፥ ደርግ ዜጎችን በውትድርና አሰልጥኖ ወደ ሀገር መከላከያ ሰራዊትነት ሲያበቃቸው ኢትዮጵያዊነታቸውን አልተነጠቁም፤ ማንም አልካዳቸውምም። እነሱ በደርግ ስርአት ውስጥ የሰለጠኑ የሀገር፣ የህዝብ ልጆች ነበሩ፡ እንጂ የደርግ ውትድርናቸው ማንነታቸውን አልፋቀውም፣ ዜግነታቸውንም አልቀየረውም። ችግሩ ባንተ የነፃ አውጪነት ዲስኩር ህዝቡን ስታደነቁር እና ስትሸነግል ያን ጊዜ ወታደር ልጇ የሞተባት፣ የጥይት የተገደለባት እናት አሁን በፍርሀት እና በጭንቀት ልጆቿን ደብቃ ስታሳድግ፣ ሳትወድ በግድ የፓርቲው አባል እንድትሆን ጓዶችሀ ሲያስገድዷት ሰምቼ፡ ኧረ ግፍ እየተሰራ ነው ብዬ ለማን ልንገር?

እስቲ ሰው የሚልህን ስማ ያንተ ነፃ አውጪነት እንደቄጤማ የብዙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ህይወት የቀጠፈ እና አካል ያጎደ ሲሆን  በየአመቱ የምታከብረው የደርግን ከሀይል መወረድ ብቻ ሳይሆን ያለቀባሪ በየሜዳው የአውሬ መጫወቻ የሆኑትን ሀገር ወዳድ ወንድሞችህን ሙት-አመት እንደሆነ ላፍታ እንኳን ብታስብ፥ የወደፊቱን የወታደር ህይወት ትታደጋለህ።
ምክንያቱም አንተም ፡ ዘላለማዊ መሆን አትችልም፥ በምድር ከተወሰነ ጊዜ በላይ መኖር አትችልም – ሟች ነህ ፣ በብርታትህ ዘመን ብዙ ጀግንነት ይሰማሃል ቆይቶ ግን ኋይል ይከዳሃል፥ ጉልበትህ ይደክማል፥ ደጋፊ ታጣለህ፥ ትወድቃለህ ፥ አትነሳም፤ ወይ በሰው ወይ አምላክ እጅ ትሞታለህ።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.