የ365 ቀናት ፈተና እና ተስፋ- የአንድ አመት ማስታወሻ

የዞን9 ጦማርያን የአነደኛ አመት ማስታወሻ

 

ከዞን9 ጦማርያን እና ወዳጅ ጋዜጠኞች

ጊዜው በጣም ይነጉዳል፡፡ ሀላፊነት የማይሰማው ስርዓት የገዛ ዜጎቹን እድሜ በእሳት ይማግዳል፡፡ ሚያዚያ 17/08/2006 ዓ.ም በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንድንውል የተደረግነው ስድስት የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን እና ሶስት ጋዜጠኞች ይሔው ከታሰርን ድፍን አንድ የእስር አመት ቆጠርን፡፡ መለስ ብለን ስናየው አጭር በሚመስለው አመት ውስጥ የሆነውንና የታዘብነውን ጠቅለል አድርገን ለማካፈል እንሞክራለን፡፡ይህ የእኛ ገጠመኝ እና ትዝብት፣ የሃሳብ ልዩነትን ማስተናገድ የሚከብደው መንግስት እስካለን ድረስ የነበረ እና የሚኖር ስለሆነየሁሉም ‹የህሊና እስረኛ › ገጠመኝ እና ትዝብት ሊሆን እንደሚችል አስታውሱልን፡፡

‹እንዳይችሉት የለም . . .›

ከያለንበት ቦታ በዘመቻ መልክ ተይዘን የፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (በተለምዶ ‹መአከላዊ›) በገባንበት ቅፅበት ነበር ስርዓቱ እንዴት እንደሚሰራ ከውስጡ መመልከት የጀመርነው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ስርዓቱ ውጪ ሆነን ከምናውቀው የባሰ እንጂ የተሻለ ሆኖ አላገኘነውም፡፡ ለምርመራውየተያዝነውን ‹‹ተጠርጣሪዎች ›› የሚያቆዩባቸው ክፍሎች መሰረታዊ የሆነውን ሰብዓዊነትን ከግንዛቤ ውስጥ ያላስገቡ እና ሕግ የማያውቃቸውይመስላሉ፡፡ ተዘግተው በሚውሉና በሚያድሩ ክፍሎች ውስጥ ተበታትነን ታጉረን በቀን ሁለቴ (ለአስር ደቂቃዎች) መፀዳጃ ቤት እንድንሄድ(ተፈጥሮን በቀጠሮ እንድንቆጣጠር ) እንገደድ ነበር፡፡ ‹የፀሃይ ብርሃንም› በቀን አንዴ ለአስር ደቂቃ እንቃመስ ነበር፡፡ይህምየሚሆነው የእኛን ‹መብት› ለማክበር ታስቦ ሳይሆን በአሳሪዎቻችን ‹በጎ ፈቃድ› ነው፡፡ ክፍሎቻችን ውስጥ ሆነን የሰማናቸውና ያየናቸው በታሳሪዎች (inmatel) የሚወሩት እና በገዛ አይናችን የምንታዘባቸው የሰቆቃ ታሪኮች ብቻ ናቸው፤ምንነቱ ያልታወቀ ነገር ‹‹እመን››በሚል የማይቀጣ የለም፡፡መአከላዊ ውስጥ እረፍት ብርቅ ነው፤ የካቴና ድምፅ በተቅጨለጨለ ቁጥር ‹‹ማነው ባለተራ›› የሚል ጭንቀትሁሉንም ሰው ሰቅዞ ይይዛል፡፡ የትኛው ተረኛ ወደ ‹ምርመራ› ክፍል ተወስዶ ይደበደብ ይሆን? የሁሉም እስረኛ ጥያቄ ነው፡፡

ሁላችንም ለጥያቄ ‹ምርመራ› ክፍሎች ውስጥ በተመላለስንባቸው ጊዜያት ሰብአዊ ክብራችንን እንድንዘነጋ እንገደድ ነበር፡፡ ፀያፍ  ስድቦችን የመርማሪዎቻችን አፍ መፍቻ የሆኑ ይመስል ከንፈራቸው ላይ ተንጠልጥለዋል፡፡ጥፊ፣ ካልቾና ስፖርታዊ ቅጣቶች የእለት ቀለቦቻችን ነበሩ፡፡ ሴቶች ሊደረግልን የሚገባ ጥበቃ ቀርቶ ሴትነታችንን መቀጣጫ የሚያደርግ አበሻቃጭ (abusive) ‹ምርመራ› ተደርጎብናል፡፡ ‹የምርመራ› ስዓቱ ገደብ የለውም ጠዋት፣ ከሰዓት፣ ማታ እና ሌሊት ሊሆን ይችላል፡፡ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ከእንቅልፍ ተቀስቅሶ ወደ ‹ምርመራ› ክፍል መወሰድ እና የደንቡን ተደብድቦ መምጣት የተለመደ ነው፡፡ ለነገሩመአከላዊ የቆየ ሰው የሚታሰርባቸው ክፍሎች የተፈጥሮ ብርሃን የማያስገቡ እና ለ24 ሰዓታት በቂ የሆነ የኤሌክትሪክ ብርሃን የማያገኙ በመሆናቸው መምሸት እና መንጋቱን እንኳን ለማወቅ በፖሊስ መነገርን ይጠይቃል፡፡ የመጀመሪያዎቹን ሶስት የእስር ወራት በዚህ ሁኔታ አሳለፍን፡፡

‹የመርማሪዎችን› አካሄድ በመመልከት በጋራ የተረዳነው አንድ ነገር ቢኖር የተጠረጠርንበት ተጨባጭ ወንጀል ወይም ማስረጃ ያልነበረ መሆኑን ነው፡፡ሆኖም መጀመሪያ ‹በተጠረጠርንበት› ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በአመፅ እና በዛቻ ለማፍረስ እና ማህበረሰብ ሚዲያን ለአመጽ ለመጠቀም የመሞከርወንጀል ወይም ኃላ በተከሰስንበት የሽብርተኝነት ድርጊትን ለመፈፀም የማሴር፣ የማነሳሳት፣ የማቀድ፣ የመዘጋጀትና የመሞከርን ወንጀል ከእኛው አፍ (በሃሰትም ቢሆን) በጉልበት ለመስማት ‹የመርማሪዎቹ› ቁርጠኝነት ወደር ያልነበረው መሆኑን ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ቤታችን፣ቢሮአችን፣ ኮምፒውተሮቻችን ፣ስልኮቻችንና ቃላችን ሁሉ ተፈትሾ የተገኘው ማስረጃ እንኳንስ ክስ ሊያቋቁም ቀርቶ የተገላቢጦሽ የእኛንንፅህና የሚመሰክሩ ሆኑ፡፡ ይሁን እንጂ ሕግ የማይገዛው አሳሪያችን ከ15 ዓመት እስከ ሞት ሊያስቀጣ የሚችል ክስ አቀረበልን፡፡ጉዳዬን ይበልጥ አስገራሚ የሚያደርገው ደሞ በምርመራው ወቅት አንድም ቀን የሽብር ተግባር እና አላማቸውን በማስፈጸም የተከሰስንባቸው ድርጅቶች አንዳቸውም አለመጠቀሳቸው ነው ፡፡

ክሱን ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ የቀጠሮ ማረፊያ ቤት (ወንዶች ወደ ቂሊንጦ ሴቶች ወደ ቃሊቲ) ተላክን፡፡ ማረፊያ ቤቶች የሕዝብ ተወካች ምክር ቤትና የሚንስትሮች ምክር ቤት ያወጡላቸው መተዳደሪያ አዋጅና ደንብ ያላቸው ሲሆን፤ ነግር ግን የሚገዛቸው ያልተፃፈ ሌላ ደንብነው፡፡ በተለይ ሴቶችን የሚያሳድረው የቃሊቲው የአዲስ አበባ የሴቶች የቀጠሮ ማረፊያ ቤት ገና ለገና ‹በሽብርተኝነት ወንጀል የተጠረጠርን›በመሆናችን ብቻ አግላይ አያያዝ በማድረግ የቀደመ ልምዱን ተግብሮብናል፡፡ ከሌሎች ተጠርጣሪዎች / ታራሚዎች በተለየ ሁኔታ የጠያቂዎቻችንንስም ዝርዝር እንድንፅፍ በማስገደድ መብታችንን ሊገድብብን፣ የምንጠየቅበትን ሰዓትም በአዘቦት ቀን ከአስር ደቂቃ እና ቅዳሜና እሁድደግሞ ከ30 ደቂቃ እንዳይበልጥ አድርጓል፡፡ ጉዳዩን ለፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ብናቀርብም የማረፊያ ቤቱ አስተዳደር ‹ችግር የለም› በማለት እውነታውን በግልጽ ሲክድ ፍርድ ቤቱም ተባብሮት አጽንቶታል ፡፡ ፍትህን የሕግ የበላይነት ከፖሊስ እጅ እንዳጣነው ሁሉበአያያዝ ረገድ ከማረፊያ ቤቱም ደጃፍ ልናገኘው አልቻልንም፡፡

ፍ/ቤቱ ‹እንደተጠርጣሪ› ለማረፊያ ቤቶቹ ያስረከበን በአደራ አቆዩልኝ ብሎ ቢሆንም፣ ማረሚያ ቤቱና የመብት ረገጣው ዋነኛ ተዋናዮች የሚመለከቱንግን ግን በጦር ሜዳ እንደማረኩት ግዳያቸው ነው ፡፡ እኛም በዚህና መሰል ለደህንነታችን ምንም አይነት ዋስትና በማይሰጥ አያያዝይህንን የመአት አመት ችለን አንድ አመት አስቆጥረናል፡፡

ምን ያሟግተናል?

በግልፅ የአሳሪያችንን መልካም ፈቃድ በወገንተኝነትና በታማኝነት በሚያገለግሉ ግለሰቦች የሚመሩትን የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ(ማዕከላዊ) ‹የወንጀል ምርመራ ቡድን› እና በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ‹ገለልተኝነት› ተሸማቀን ስናበቃ የተጋፈጥነው አንበሳውን  የፍትህ ስርዓታችንን ነው፡፡

ወንጀልን ሊያቋቁም የሚችል ምንም አይነት ማስረጃ በሌለበት በወንጀል መጠርጠራችንና መከሰሳችን ከሁሉም ቀዳሚው በደል እንደሆነ ይሰማናል፡፡ነገር ግን ስለፍትህ አውርተናል ጠይቀናል ተከራክረናልና የኖርንበትን ታላቅ አላማ እኛው ፈልገን የፍትህ በርን እያንኳኳን እንገኛለን፡፡‹‹ለምን ተጠረጠርን?››‹‹ለምንስ ተከሰስን?›› ብለን ፍትህን ከመሻት ራሳችንን ሳናቅብ የቀረበብን ክስ እንደ ክስ ሊቆም የማይችልእንደሆነ ሕጋዊና ሙያዊ መቃወሚያ አቅርበን ፍርድ ቤቱም ‹ተቀብዬዋለሁ ግን አልተቀበልኩትም› በማለት ልንረዳው ያልቻልነውን ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ከእስራችንም በፌት የምንታወቅበትን የአገሪትዋን ህግ በመጠቀም መብቶቻችንን የመጠየቅን ሂደት አጠናክረን የምንገፋበት ተቋማቱ ገለልተኛ ናቸው ብለን ስለምናምን ሳይሆን ከተቋማቱ ጀርባ ላለው ፍትህ እና ህግ የበላይነት ያለንን ቁርጠኛነት ለማሳየትምጭምር ነው፡፡

ከሣሻችን አለኝ የሚለውን ‹ማስረጃ› በከፊል ከእኛ ከተከሳሾች ደብቆ እንኳን የተባለውን ‹ማስረጃ› ለማድመጥ የአንድ አመት ጊዜ መጠበቅ ነበረብን፡፡የዘገየ ፍትሕ እንደተነፈገ ይቆጠራል መባሉን ከሳሻችን እንደሚያውቅ ብናውቅም እኛ ግን የዘገየውን ‹ፍትሕ› እንኳን ለመጠየቅ የሚያስችልትዕግስት አላጣንም፡፡

አሁንም ፍትሕ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዓይነተኛ መለያ ቀለም ነው ብለን እናምናለን፡፡ ፍትሕ ይኖር ዘንድ ገለልተኛ ተቋማት መኖራቸው ደግሞ የግድ ነው፡፡ ተቋማት ለተቋቋሙበት ዓላማ ከመኖር ይልቅ ታማኝነታቸውን ለስርዓቱ ሹማምንት ማድረግ ሲጀምሩ ፍትሕ አስቸጋሪ ፈተናውስጥ ይገባል፡፡ ፍትሕ እኛ በታሰርንባት ኢትዮጵያ ይሕ ፈተና እንደገጠማት ይሰማናል፡፡እንግዲህ የኛ ተስፋና ጥበቃም ከዚህ እውነትየሚመነጭ ነው፡፡

ወንጀላችንን ፈልገን ማግኘት አልቻልንም በህግ ፌት ንጹህ ነን ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ይሕ ንፅሕናችን መቼና እንዴት እንደምንፈታ አይነግረንም፡፡አንድ ነገር ግን እርግጠኞች ነን፡- እውነት ከኛ ጋር መሆኗን፡፡

በተስፋ የሚያቆመን . . .

እኛን ከአገራችን ብቻ ሳይሆን ከመላው አለም የዴሞክራሲ ቤተሰብ ጋር ያስተሳስረናል ብለን የምናምነው ዕሴት ሐሳብን በነፃ የመግለፅ ነፃነት ላይ ያለን ፅኑ እምነት ነው፡፡ ሰዎች ሀሳባቸውን ያለምንም ጣልቃ ገብነትና ፍርሃት መግለፅና መደማመጥ ሲችሉ አገራችንን ጨምሮ በዓለማችን ያሉ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን መቅረፍ የሚችሉ ሀሳቦችና መነሳሳቶች መፍጠር ይችላሉ የሚል እምነት ከመታሰራችን በፊትም ይሁን በኋላ በውስጣችን አለ፡፡ የታሰርነውም ይህንን ተፈጥሮአዊ ነፃነታችንን ለመጠቀም ሙከራ ማድረግ ስንጀምር ነው፡፡ በየትኛውም አምባገነናዊ ስርዓት ውስጥ እውነትን ለጉልበተኞች መናገር ዋጋ ያስከፍላል፡፡እኛም ሐሳባችንን በነፃነት ስለመግለፅ እየከፈልን ያለነውዋጋ የማይከብደን የነገይቱ ኢትዮጵያ ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ የተሻለች ትሆናለች የሚል ተስፋ በማድረጋችን ነው፡፡

የሚያበረታን . . .

የመታሰራችን ዜና ከተሰማ ጀምሮ ብቻችንን አልታሰርንም፡፡ ብዙዎች አኛን ከከለለን አጥር ውጪ አብራችሁን ታስራችኋል፡፡ ስለዚህ የእስር ቤት ጌጥ የሆኑት የመረሳትና ተስፋ የማጣት ስጋቶች እንዳይጎበኙን ያደረገንና በብርታት ያቆመን የእናንተው በእሳት የተፈተነ አብሮነት ነውና ሁላችሁም ምስጋና ይገባችኋል፡፡

እምነታችን እዳ ሆኖባችሁ ከታሰርንበት ደቂቃ አንስቶ የመንፈስም፣ የአካልም ዕረፍት ሳያሻችሁ እየደከማችሁ ላላችሁ ቤተሰቦቻችን፣ በፈተናችን ሰዓት ሕመማችንን አብራችሁ ለታመማችሁ ወዳጆቻችን (friends indeed)፣ ከታሰርንበት ጊዜ ጀምሮ ንፅህናቸንን ተረድታችሁ ጉዳያችንንእንደ ጉዳያችሁ እየተከታተላችሁ ላላችሁ እና የመንፈስ ድጋፋችሁ ላልተለየን አገር በቀል እና አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን፣ ሰብአዊነትናየዴሞክራሲ ተቆርቋሪዎች ስለድካማችሁ ምስጋናችን የበዛ ነው፡፡ የማረፊያ ቤት ቆይታችን አዲስ አይነት የህይወት ልምድ የምናገኝበትናየምንማርበት ይሆን ዘንድ አብራችሁን በማረፊያ ቤት የነበራችሁ/ያላችሁ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን እናንተም ምስጋናችን ይድረሳችሁ፡፡እንዲሁም ይህን በሕግ አግባብ ያልተመሰረተ ክስ በሕግ አግባብ እንዲቋጭ ያላሰለሰ ጥረት እያረጋችሁ ያላችሁት ጠበቆቻችንና ሌሎቻችሁም. . . ምስጋናችን ከልባችን የፈለቀ ነው፡፡ ሁላችሁም የምንበረታው በእናንተ ነውና እጅግ በጣም እናመሰግናለን፡፡

#FreeZone9bloggers  #FreeEdom  #FreeTesfalem  #FreeAsemamaw #Ethiopia

Zone9

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.