ከሮቤል ወሬ 〉ወደ ዱብ፡ ዱብ

ሀገር ሰላም ነው ብለን ውይ ይቅርታ ለካ ሀገር ሰላም አልነበረም፤ ኢንተርኔት ይሰራል ብለን የዜና መስኮቶቻችንን ስንከፋፍት የፌስቡኩ ወሬ ከሰላማዊ ሰልፍ ወደ ሮቤል ኪሮስ የዋና ውጤት ላይ አተኩሮ ነበር። ያው ዜናውን አነበብኩና ወደሌሎች አለማቀፍ ወሬች ሳመራ እዛም እርሱ ነው፤ በጣም ገርሞኝ ሳነብ ቆየሁ። አንዴ ባማርኛ ሌላ ጊዜ በእንግሊዝኛ የስድብና የትችት መዓት በሮቤል ኪሮስ ሀብቴ ላይ ሲወርድ በዓይኔ ሳነብ ከቆየሁ በኋላ እኔም በተራዬ ልክ ልኩን ብዬ የውስጤን አወጣሁና ወጣልኝ።
ከዛም መሸ፡ ነጋ፣ መሸ፡ ነጋ፤ ለካ ሀበሻውም ፈረንጁም አቤልን ሰድበው አልወጣላቸውም። በሮቤል ላይ ከተሰነዘሩት ትችቶች ያልተስማማሁበት ነገር አንድም የለም።
ከአቤል ትችቶች በጥቂቱ:
  1. ብቃት የሌለው የነፃ ዋና ተወዳዳሪ
  2. ኢትዮጵያን በየትኛውም ስፖርት መወከል የለበትም (ምናልባት ነፃ ትግል)
  3. ውክልናውን በዝምድና ማግኘቱ ደግሞ ይበልጥ ከሁሉ ታናሽ አድርጎታል
  4. ወዘተ
ከአቤል ድሎች ብቸኛው:
  1. የኢትዮጵያውያን የሁል ጊዜ የቀጫጫነት ተምሳሌት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ቦርጫምነት ቀይሮታል።

ለአቤል አምሳዮች (ለወንዶች ብቻ)

አቤልን ለመተቸት ብዙ ሊባል ይችላል፤ ነገር ግን ስንቶቻችን ነን የአቤልን አይነት የሰውነት አቋም ይዘን ለትችት የበቃነው? እንደው ስፖርት ከተሰራስ ስንት ጊዜ ሆነው? ጠዋት ተነስቶ ስፖርት የሚሰራውስ የትኛው የአዲሳባ ሰው ነው? ወይስ የየትኛው ዋሽንግተን ዲሲ ጂም ነው አባልነትህ?
ቢያንስ እንኳን አቆጣጠሩ ባይገባኝም ሮቤል በቀን (ጠዋት3000ሺ + ማታ 3000ሺ) = 6000ሺ ይሰራል። እንደብርሌ የተጎለተ ቦርጭ ተይዞ አቤልን ማንኳሰስ እጅጉን ከባድ ጥፋት ነው፤ ያው ስሜት አይሰጥማ ጃል። ፈረንጆቹ እኮ የአቤልን አይነት ሰውነት እንደጤና አይመለከቱትም፤ ለዛም በየቀኑ ስፖርት ቤት ይሄዳሉ፣ በየፓርኩ ይሮጣሉ፣ አመጋገብ ያስተካክላሉ፡ ወዘተ።

ፍልፍሉ በኢቢኤስ
ሀበሻው ግን የአቤልን አይነት ሰውነት እንደ ምቾትና የተሻለ ኑሮ ማሳያ ይመለከተዋል፤ ለዚህም አቤል ከአብዛኛው የሀበሻ የአዋቂ የሰውነት ቁመና ጋር የሚመሳሰለው።
ያው አቤል ኪሮስ እንደ ስፖርተኛና ሙሉ ሰውነቱ በካሜራ እንደሚቀረፅ ተወዳዳሪ የተስተካከለ ቁመና ቢኖረው የተሻለ ነበር። ነገር ግን ፈረንጆቹ በአቤል የሰውነት አቋም ላይ ካቀረቡት ትችት ልንማር የሚገባን የአብዛኛው የሀበሻ የአዋቂዎች አቋም ጤናማ ያይደለና በተለያዩ የሰውነት እንቅስቃሴዎች ልናስተካክለው እንደሚገባን ነው። የአመጋገብ ስርዓታችንን ማስተካከል ደግሞ እጅጉን ተገቢ የሆነ መፍትሄ ነው ባይ ነኝ።
እንዲህ መካሪ ያደረገህ ማነው ካላችኑኝ፡ ቅጥነቴ ብዬ ልሰናበት።

የቄሳርን ለቄሳር የህዝብን ለህዝብ

ኢትዮጵያ የህዝብ መንግስት ያስፈልጋታል!
በ2007ቱ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምርጫ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በምርጫው ላይ ከፍተኛ ድምፅ አግኝቻለሁ እንዲያውም በትክክል 100% የህዝብ ደምፅ አገኝቻለሁ ሲል ቀልድ ወይም ‘አፕሪል ዘ ፉል’ መስሎን እውነተኛውን ዜና ስንጠብቅ ይኧው አንድ ዓመት አለፈን። ይባስ ብሎ አሸንጉሊት እና ማሰብ የተሳናቸውን ባለስልጣናት አበዛልን፤ መቸም ለዚህ ተመስገን አይባል። ☺በዘር፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በሀይማኖት እና በብዙ የተለያዩ መንገዶች ህዝብን ከህዝብ መለየት፣ ወዳጆችን ማጋጨት፣ ቂመኞችን በማበረታታና በማደራጀት በወገናቸው ላይ ግፍ እንዲፈፅሙ ማድረግ፤ በቃ በማንኛውም መንገድ ልዩነትን ማስፋት የሁልጊዜ አጀንዳው የሆነ መንግስት ይህችን ታላቅ እና ታሪካዊ ሀገር በብረት እየመራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ መንግስት የህዝብ መንግስት አይደለም!
በቅርብ ጊዜያት ግን በተለያዩ መንገዶች በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መንግስት እንዳልሆነ እየተመለከትን ያለንበት ሁሌታ ነው ያለው። ለዚህም ብዙም ሳንርቅ በኦሮሚያ ለአመታት እየተካሄደ የነበረው የህዝብ ጥያቄ (በሰላማዊም በአመፃዊም)፡ ትልቅ ማሳያ ነው። በተጨማሪም ከቅርቡ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የህዝብ ድምፅ እየጎላና እየተስተጋባ ይገኛል። ለምሳሌ በጎንደር ከተማ የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ከንግር በላይ ነው፤ ምክንያቱም ህዝቡ መብቱን በሀይል ሲከለከል በሰላማዊ መንገድ ጥያቄዬን ሳላሰማ አመለስም በማለት ወደ አደባባይ በመውጣት ተኝተው ለነበሩት የማንቂያ ደውል ተባባሪ ለፈለጉት ደግሞ መልካም ዜናን በማወጅ ለአዲሱ ሰላማዊ ትግል ትልቅ አስዋፅኦ አድርጓል።
df31312b1e90443589d625acb5c29f17_18
መንግስት የህዝብ ነው፤ ህዝብ የመንግስት አይደለም።
የቄሳርን ለቄሳር የህዝብን ለህዝብ!ለጊዜው የቄሳሩን ትተን የህዝቡን እናውራው። ብሶት የወለደው የህወሓት ሰራዊት ሀገሪቱን ከወታደራዊው ደርግ በመንጠቅ ወደሌላ ወታደራዊ አገዛዝ ቀየረው። ለዚህም እንዲረዳው የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ይህችን ታላቅ ሀገር ከላይ በጠቀኳቸው መንገዶች ከፋፈላት፤ ይኧውም ለ25 ዓመታት በስልጣን ላይ ይገኛል። ከታሪካዊው የትግራይ ህዝብ የወጣው ነገር ግን ታሪካዊ ስሀተት እየሰራ ያለው መንግስት የአብላጫውን የትግራይ ህዝብ ሊወክል ይችል ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ምንም ክፋት የለውም። ነገር ግን በመላው ሀገሪቱ ላይ ለመግዛት እንዲመቸው ኢህአዴግ በሚል ሌላ ቅፅል ስም ወደ ምርጫ በመምጣትና በራሱ ማጣሪያ የተለያዩ ብሄሮችን ይወክላሉ ያላቸውን የህዝብ መሰል የፖለቲካ ፓርቲዎች በማቋቋም መንግስት መሰረተ፤ በአምስት አመት አንድ ጊዜ ደግሞ በራሱ ምርጫ አሸናፊነቱን እንዲነግረው የራሱ የሆነ የምርጫ ቦርድ አቋቋመ።በቃ ምን አለፋቹ ሁሌም ምርጫ አለ ሁሌም አንድ አሸናፊ አለ፤ ስሙም ህወሓት ይባላል። ለምን እንደሆነ እንጃ ብቻ ሁሌም ቢሆን በጫካ ስሙ መጠራቱን ይወደዋል።ታዲያ የህዝብ ሊሆን የተገባው ነፃነት ላይ ማን እየተጠቀመበት ነው? ደም አፍስሰን ነው እዚህ የደረስነው ይሉናል፥ ታዲያ የህዝብን ደም ለምን ታፈሳላቹ? የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ነው የመጣነው ይሉናል፥ ታዲያ የየትኛውን ህዝብ ጥያቄ ነው የመለሳችሁት?ነው ወይስ የታላቋን የትግራይን መንግስት ለመመስረት በቂ የሆነ የህዝብ ቂም እያከማቻችሁ ነው?
ethiopians-call-for
የህዝብን ስልጣን ወደ ህዝብ!
የትግራይ ህዝብ የመረጣችሁ ምርጫ ኖሮት ሳይሆን ቋንቋውን የሚናገርለት ከራሱ ጓሮ የበቀለ የአመፅ ቡድን አንድ ብቻ ስለነበረ ነው፥ እርሱም ህወሓት ይባላል፤ ሲተነተን ህዝበ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ፦ የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ እንደማለት ነው። ስለዚህ አማራጭ አለበረም ቶሎ ተቀባይነት አገኘ። ነገር ግን በየጊዜው የተለያዪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከትግራይ ህዝብ የወጡ ነገር ግን በህወሓት የተደመሰሱ ብዙ ናቸው። ወደታላቋ ሀገራችን ስንመጣ ግን በተገኙት አጋጣሚዎች፣ ምርጫዎች፣ የህዝብ ስብሰባዎች ሁሉ መሪው መንግስት የህዝብ ድጋፍ እንደሌለው እና በሀይል ሲገዛ እንደኖረ ለማረጋገጥ የማይረሱ የቅርብ ጊዜ ዜናዎችን መመልከት በቂ ነው።
በቃ ማለት በቃ ነው!
ይህ መንግስት አሁንም የህዝብን ድምፅ ለመስማት ዝግጁ አይደለም እንዲያውም እየጨቆነና ትላንት ካደረጋቸው የጭካኔ ተግባራት ይልቅ ብሶበት እና ጨምሮ እየተገኘ ነው፤ እንዲያውም ብዙዎች ካለፈው ወታደራዊ መንግት ጋር ያነፃፅሩታል። ሰሚ ካለ ይስማ፥ መንግት የህዝብ ነው እንጂ ህዝብ የመንግስት አይደለም።
የፅሁፉ ዋና አላማ የህዝብን ሀሳብ ለመጋራት እንጂ የየትኛውንም የፖለቲካ ፓርቲ ሀሳብ ለመደገፍ አይደለም።