የምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሥራ መልቀቂያ አስገቡ

በለውጥ ሒደት ላይ መሆኑና አዳዲስ አሠራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሆነ የተገለጸው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤርሚያስ እሸቱ፣ ያልተጠበቀ ነው የተባለ የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸው ታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ለመምራት ሦስተኛው ሰው የነበሩት አቶ ኤርሚያስ ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ምክንያት የሆናቸው ጉዳይ አልታወቀም፡፡ የምርት ገበያው የዳይሬክተሮች ቦርድ ግን የሥራ መለቀቂያ ጥያቄያቸውን ተቀብሎ፣ አዎንታዊ መልስ እንደሰጣቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ሆኖም አቶ ኤርሚያስን የሚተካ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እስኪገኝ ድረስ፣ በኃላፊነታቸው እንዲቆዩ መደረጉን ምንጮች አመልክተዋል፡፡

ምርት ገበያው አዳዲስ አሠራሮች ተግባራዊ እያደረገ መሆኑ እየተገለጸና እሳቸውም በተለይም ለውጡን ለመምራት ያሏቸውን ዕቅዶች እያሳወቁ ባሉበት ወቅት፣ ሳይታሰብ የሥራ መልቀቂያ አስገብተዋል መባሉ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

አንደ ምንጮች ገለጻ፣ ምርት ገበያው ለውጥ ለማድረግ ቦርዱ ሥር ነቀል ግምገማ እያካሄደ ነው፡፡ አቶ ኤርሚያስንም ጠንከር ብሎ ገምግሟል፡፡ የሥራ መልቀቂያ ጥያቄ ቀረበ የተባለውም ከዚህ ግምገማ በኋላ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሥራ አመራር ቦርድ የምርት ገበያውን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም በጥብቅ መገምገሙ ተገልጿል፡፡ እስከ ምሽት አምስት ሰዓት ድረስ እየተቆየ የተካሄደው ግምገማ አቶ ኤርምያስን ያካተተ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከግምገማው የሚገኘው ውጤትም የተቋሙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በቦታቸው ላይ መቆየት አለመቆየታቸው ሊወሰን የሚችል ሊሆን እንደሚችል፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ጠቁመዋል፡፡

በምርት ገበያው ለውጥ ለማምጣት ጠንካራ ጎኖቹንና ድክመቶቹን ለመለየት ግምገማው እየተካሄደ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ይህ የምርት ገበያው ሰሞነኛ ግምገማ ከአሁን በፊት በተቋሙ ያልታየ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ላይ ከተደረገው ግምገማ በኋላ ሁሉንም ሠራተኞች የያዘ ውይይት ይደረጋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡

በአቶ ኤርሚያስ የሥራ መልቀቂያ ጥያቄ ላይ የምርት ገበያው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ለጊዜው አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ አቶ ኤርሚያስን ለማነጋገር ሪፖርተር ለቀናት በተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካም፡፡ በሥራ ገበታቸው ላይ እንዳሉ ግን ታውቋል፡፡

የ42 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ ኤርሚያስ ምርት ገበያውን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲመሩ የተሰየሙት ታኅሳስ 23 ቀን 2007 ዓ.ም. ነበር፡፡ ምርት ገበያውን ከመቀላቀላቸው በፊት የዘመን ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሲያገለግሉ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከ20 ዓመታት በላይ የእንግሊዝ ቆይታ በኋላ ወደ አገር ቤት ተመልሰው ኑሯቸውን የጀመሩት በ1994 ዓ.ም. ነበር፡፡ በውጭ ቆይታቸውም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታወቁት አይቢኤምና አልካቴል ማክሮ ስትራቴጂ በተባሉ ኩባንያዎች ውስጥ ሲሠሩ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያን ከምሥረታው ጀምሮ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ያገለገሉት እሌኒ ገብረ መድኅን (ዶ/ር) ኃላፊነታቸውን ሲለቁ፣ በእሳቸው እግር የአቢሲኒያ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ አንተነህ አብርሃም ተክተዋቸው ነበር፡፡ ሆኖም አቶ አንተነህ ከጤና እክል ጋር በተያያዘ ምክንያት ለወራት የያዙትን ኃላፊነታቸውን ሳይታሰብ ከለቀቁ በኋላ በአቶ ኤርሚያስ መተካታቸው አይዘነጋም፡፡.

ምንጭ፥ ሪፓርተር

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.