አቶ አዲሱ አረጋ በፊስቡክ ገፃቸው ለሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የላኩት ደብዳቤ

ይድረስ ለሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ሰሞኑን ከተከሰተዉ ችግር ጋር አያይዞ በትናንትናዉ ዕለት በአማርኛ ቋንቋ መግለጫ አዉጥቷል፡፡ የወጣዉ መግለጫ እጅግ በጣም አሳፋሪ እና ሀላፊነት በጎደለዉ መልኩ የቀረበ ነዉ፡፡ መግለጫዉ አሁን ያለዉን ችግር ከማርገብ ይልቅ ወደ ሌላ አቅጣጫ ሊወስድ የሚችልና ሀገርን ከሚያስተዳድር ትልቅ የመንግስት መስሪያ ቤት ይሰጣል ተብሎ የማይጠበቅ አሳፋሪ መግለጫ ነዉ፡፡ የወጣዉ መግለጫ የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የተጣለበትን ህዝባዊ እና መንግስታዊ ሃላፊነት ከመሸከም አንጻር ያለበትን ደካማ ቁመናና ዝቅተኛ ደረጃ ፍንትዉ አድርጎ የሚያሳይ ነዉ፡፡

ከመግለጫዉ ስህተቶች የሶማሌ ክልላዊ መንግሰትን የፌዴራል ስርዓቱ ብቸኛ ዘብ እና ጠባቂ እድርጎ የማቅረቡ ጉዳይ ነዉ፡፡ በእኛ እምነት አሁን ላለዉ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓት ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች እኩል መስዋዕትነት የከፈሉበት የትግላቸዉ ዉጤት ነዉ፡፡ ስለሆነም አሁን እየገነባን ላለነዉ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓት ዘቦች ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ናቸዉ፡፡ የመግለጫዉ ሀሳብ በተጨባጭ ተግባር የሚገለጽ ቢሆን ኖሮ ደግሞ እሰየዉ ነበር፡፡ አንድ የፌዴራሊዝም ዘብ ነኝ የሚል መንግስት በምን ስሌት ልዩ ሃይል አደራጅቶ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት ይፈጽማል? ሰሞኑን በተፈጠረ ግጭት እንኳ ስንት ሰላማዊ ዜጎች በኦሮሞነታቸዉ ብቻ ቄያቸዉን ጥለዉ እንዲሰደዱ እየተደረገ አይደለምን? ከዚህ አንጻር የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የክልሉን መንግስት የፌዴራሊዝም ዘብ ነኝ ብሎ ራሱን ማቅረቡ ከተግባሩ ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የቢሮዉ መግለጫ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልልን “የኦሮሞ ክልል” ብሎ ከህገ መንግስቱ ዉጪ መሰየሙ ነዉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ “የኦሮሞ ክልል” የሚባል ክልል የለም፡፡ መግለጫዉ ይህን አጻጻፍ የተከተለዉ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልልን “የኦሮሞዎች ብቻ” እንደሆነችና ሌሎች የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችን የማታቅፍና አግላይ አስመስሎ ማቅረብ የሞከረበት አደገኛ ተልዕኮ ያለዉ አጻጻፍ ነዉ፡፡ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እምነት የኦሮሚያ ክልል የሁሉም ኢትዮያዊያን ናት፡፡ ለዚህ ደግሞ የክልሉ፣ ስያሜ “የኦሮሞ ክልል” የማይሆንበት ምክንያት ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች በወንድማማችነት እና በአንድነት በፍቅር የሚኖሩባት ክልል እንደሆነች ምስክር መጥራት አያስፈልገንም፡፡

ሶስተኛዉ መሰረታዊ ስህተት የክልሉን መንግስት በአሸባሪነት እና በኦነግነት መፈረጁ ነዉ፡፡ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አመራሮች በኢትዮጵያ አንድነት እና በህዝቦች ወንድማማችነት ላይ የማያወላዉል ጽኑ አቋም እንዳለን መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ምስክራችን ነዉ፡፡ ኦሮሚያ እና የኦሮሞ ህዝብ የኢትዮጵያ አንድነት ምሶሶዎች ናቸዉ፡፡ የክልሉ አመራሮችም ለፌዴራላዊ ስርዓታችን ማበብና መጎልበት የህዝቦች ወንድማማችነት እና እኩል ተጠቃሚነት እንዲሰፍን ለማድረግ እየታገሉ መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉ ዉድ የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆች እንጂ በአሸባሪነት እና በኦነግነት የሚፈረጁ አይደሉም፡፡ መግለጫዉ ከዚህ አንጻር ሀላፊነት በጎደለዉ አግባብ የተጻፈና ወንጀልም ጭምር በመሆኑ ህገ መንግስቱን ተከተለን ህጋዊ እና አስተዳደራዊ መንገድ የምንጠይቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ ከዚህ ባለፈ የኦሮሞ ተወላጆችን እና የክልሉን አመራሮች በኦነግነት ሌብል ማድረግ ለማሸማቀቅ መሞከር ከበርካታ አመታት በፊት ሲደረግ የነበረ አሁን ግን ጊዜዉ ያለፈበት ተራ ሌብሊንግ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

የመግለጫዉ ሌላኛዉ ይዘት ግጭትን የሚያባብሱ አደገኛ ቃላት እና በተጋነኑ ዉሸቶች መሞላቱ ነዉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ሰሞኑን በተከሰተዉ የጸጥታ መደፍረስ ክቡር የሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ በዚህ ረገድ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ኦሮሞም ይሁን ማንም ሰዉ መሞት የለበትም ብሎ ያምናል፡፡ በሰሞኑ ሁኔታ ከሁለቱም ወገን ህይወታቸዉ ላለፉት ዜጎች የተሰማዉን ጥልቅ ሀዘን ይገልጻል፡፡ ከዚህም በላይ በንጹኃን ዜጎች ላይ የህይወት ማጥፋት አና አካል የማጉደል ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ለህግ መቅረብ አለባቸዉ ብሎ ያምናል፡፡ ከዚህ በተረፈ ሰሞኑን ስለነበረዉ እዉነታ ሀቁን ለህዝባችን መግለጹ አስፈላጊ ነዉ፡፡ መስከረም 1/2010 ከጉርሱም ወደ ወደ ሀረር እየተጓዙ ያሉ ሰላማዊ የኦሮሞ ተወላጆችን የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የጸጥታ አካላት ቦምባስ ከተማ ኬላ ላይ ይዘዉ ያስራሉ፡፡ እነዚህ ታሳሪዎች አቶ ሳላህ መሀመድ (የጉርሱም ወረዳ አስተዳዳሪ የነበረ)፣ አቶ ታጁዲን ጀማል እና ሌሎች ሌሎች ሁለት ሰዎች፣ በነጋታዉ በደረሰባቸዉ ድብደባ መሞታቸዉ ተሰማ፡፡ ይህ ሰላማዊ ሰዎች ከላይ ተፈጸመዉ ግድያ የምስራቅ ሀረርጌ ነዋሪዎችን በማስቆጣቱ በምስራቅ ሀረርጌ ዞን አወዳይ፣ ደደር፣ ቆቦ እና መልካ ራፉ ከተሞች ያልተጠበቀ የህዝብ ቁጣ እና ሰልፍ አስከተለ፡፡ በተለይ አወዳይ የነበረዉ ሰልፍ ወደ ግርግር ተሸጋገረ፡፡ የበተፈጠረዉ ግርግርም የ18 ሰዎች ህይወት ሊያልፍ ችሏል፡፡

በዚህ ግርግር ዉስጥ ህይታቸዉ ካጡ 18 ሰዎች 12 የሶማሌ ተወላጅ ወንድሞቻችን ሲሆኑ 6ቱ ደግሞ የጃርሶ ጎሳ ተወላጅ ኦሮሞዎች ናቸዉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ድንበር ላይ እየተፈጸመ ካለዉ ጥቃት ጋር ምንም ተያያዝነት የሌላቸዉ፣ በላባቸዉ ሰርተዉ የሚያድሩ ሰላማዊ ዜጎች ናቸዉ፡፡ በዚያ ግርግር የእነዚህ ወንድሞቻችን ህይወት ማለፍ በእጅጉ አሳዝኖናል፡፡ በድርጊቱ ተሳትፎ አላቸዉ ተብለዉ የተጠረጠሩ ከ200 ሰዎች በላይም ቁጥጥር ስር ዉለዉ ምርመራ እየተደረገባቸዉ ነዉ፡፡ እዉነታዉ ይህ ሆኖ ሳለ የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ይህን ጉዳይ ግጭትን በሚያባብሱ ስሜታዊ ቃላት እና ዉሸትን ጨምሮ አጋኖ ማቅረብ ግጭቱን ከማባባስ ያለፈ ምንም ጠቀሜታ አይኖረዉም፡፡

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ስንገልጽ እንደነበረዉ የኢትዮጵያ ሶማሌ እና የኦሮሞ ህዝቦች ወንድማማች ህዝቦች ናቸዉ፡፡ በጋብቻ እና በደም የተሳሰሩ፣ ተመሳሳይ የአኗኗር ዘይቤ፣ ተመሳሳይ ስነ ልቦና ያላቸው ህዝቦች ናቸዉ፡፡ አሁን እየተከሰተ ያለዉ የሰላም መደፍረስ የሁለቱ ህዝቦች ፍላጎት እንዳልሆነ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህ ግጭት ጀርባ ያሉ አካላት ተጣርተዉ ወደ ህግ እንደሚቀርቡና የስራቸዉን ዋጋ እንደሚያገኙ ምንም ጥርጥር የለንም፡፡
የኢትዮጵያ ሶማሌ እና የኦሮሞ ህዝቦች ወንድማማችነት ለዘለዓለም ይኑር!

መስከረም 4/2010

ፌስቡክ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.