ሃበሻ ድንቅ ህዝብ ነው (ሄኖክ የሺጥላ)

ሀበሻ ድንቅ ህዝብ ነው ።

የሚያስደንቅ ለማለት ነው። ሀበሻን የመሰለ የትም የለም ። ለምሳሌ ህንዱ ፥ ቻይናው ፥ ሱማሌው ፥ ቱርኩ ፥ ቬትናሙ ፥ ፊሊፒኑ ከኮሌጅ እስከ መስሪያቤት ይረዳዳል ፥ አንዱ ላንዱ ስራ ለማግኘት ይተጋል ፥ በስራ ላይም ቢሆን ጉዱን ይደባበቃል ፥ ይተጋገዛል ፥ ይቦዳደናል ። ሀበሻ ግን እንዴት ሀበሻን መርዳት እንደሌለበት ያስባል ። የተሻለ ነገር ሲያገኝ እንዴት ብቻውን ሊጠቀም እንደሚችል ያሰላል ። እንዴት ሌላ ሀበሻ አብሮት እንደማይሆን ሳይቀር ይተልማል ።

ሀበሻ ድንቅ ህዝብ ነው ። ለባንዲራው እንጂ ለወንድሙ ፍቅር የሌለው ። ለእስክስታው እንጂ እስክስታ ለሚለው ቁብ [ ግድ ] የማይሰጠው ። ተቸግሮ ፥ጥሮ እና ግሮ ጥሩ ቦታ ሲደርስ ፥ ያለፈበትን ከማመስገን ይልቅ በሌጣነት ፥ በድህነት ዘመኑ የሚያውቁትን ፥ የረዱትን ማየት የማይሻ ፥ ሲቻል መናቅ የሚፈልግ ፥ ግን ደሞ አኩሪ ባህል አለኝ እያለ የሚታበይ ህዝብ ነው ።

ስለ ጀግንነት የሚያቅራራ ፥ የሚያጓራ፥ ጀግንነትን ግን የሚፈራም ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እና በጥልቀት ማንነታችንን ሳልዘረዝረው ፥ ሀበሻ ግን ኩሩ ህዝብ ነው እላለሁ። የወጣለት ኩሩ። በየአረብ አገሩ የሚረገጥ ኩሩ ፥ መብቱን የነጠቁቱን ተናንቆ መብቱን ከማስከበር ይልቅ ፥ ለአንድ አይነት ሞት በባህር ውሃ መሞትን የሚመርጥ ኩሩ ። አገሩ ሻይ ቤት ተቀጥሮ መስራት ውርደት የሚመስለው ፥ በሰው አገር የሽማግሌ ፈረንጅ ሽንት ጨርቅ [ ዳያፐር ] መቀየር ምንም የማይመስለው ኩሩ ህዝብ ነው ሀበሻ ! በድብቅ መዋረድ ፥ በድብቅ መገረድ ፥ በድብቅ ማጎብደድ ህቅም ስቅም የማይለው። አበሻ ሲያየው ግን በሚሰራው የሚያፍር ። ፓርኪንግ እየሰራ ፥ ለፓርከር ሃኒፊን ዲዛይነር ነኝ ብሎ የሚያወራ ፥ አራት እና አምስት ሺ ዶላር ይዞ አገሩ ገብቶ ፥ በቁምጣ ሃይላንድ እየጠጣ ከተማውን የሚያምስ ብሶተኛ !
አበሻ እኮ ለፋሲካ በገዛውና ነገ በሚያርደው በግ ስባት የሚፎካከር ነው። በአገር ባህል ልብሱ ውበት ጠሎት ቤት የኔ ይበልጥ የሷ እያለ የሚገዳደር ነው ። አበሻ እኮ ልጆቹን እንግሊዘኛ በማስተማሩ ብቻ ሳይሆን [ ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖሩ ] አባታቸውን ዳዲ ብለው የሚጠሩ ልጆቹ በማሳደጉ የሚጀንን ነው ። ዛሬ አገሬ ውስጥ እንደ አሸን የፈሉት መዋዕለ ህፃናቶች ትልቅነታቸው የሚለካው በኢትዮጵያዊ ይዘታቸው ሳይሆን ነጮችን ለመምሰል በሚያደርጉት ጥረት ባላቸው ቅርበት እና ርቀትስ አይደለም ወይ ? የመዝናኛ ቦታዎች ፥ ፀጉር ቤቶች ፥ ስፖርት ቤቶች እንዴት አበሻ መምሰል እንደሌለባቸው አይደለም ወይ የሚታሰበው ። እንግሊዘኛ መናገር የተቃራኒ ፆታን ልብ ለመስለብ እንደ አንድ አብይ መሳሪያ የሚጠቅም ነገር አይደለም ወይ ? ይህ የኛ አገር ነው ። ይህ የኛ ማንነት ነው !

ቤተ እምነቶች « ከሱዑዲ አረቢያ 500 ሪያል ስለት ገብቷል » እልል በሉ አይሉም ወይ ? ከዱባይ ይህን ታህል እልል በሉ አይሉም ወይ ? የት ነው ሞራሉ እና ማንነቱ የሞተው ? መቼ ነው መሻገት የጀመርነው ? አበሻ ባክህ ድንቅ ህዝብ ነው ! ለምለም አገር ያለው ግን የሚርበው !

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.