⚡ትንቢትና የነቢያት እንሴን በተመለከተ

⚡ከሰሞኑ በማህበራዊ ድህረገፆች የተዘዋወረው የኔ አቋም በሚል ሁሉም በግድግዳው የለጠፈው ፅሁፍ

እኔ ወንጌላዊ ክርስትና አማኝ ነኝ። በዚህ ጽሑፍ የትንቢትና የነቢያት አገልግሎትን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረገ ግላዊ አቋሜን ለማንጸባረቅ እሞክራለሁ።

ይህንን ለማድረግ የተነሣሁበት ዋነኛው ምክንያት ሰሞነኛው የነቢያትና የሐሰተኛ ትንቢቶች ውዥንብር ነው። እኔ በወንጌል እንደሚያምን አንድ ክርስቲያን፣ ከአብና ከወልድ የተካከለ የሕይወት ሰጭና ጌታ በሆነ አምላክ በመንፈስ ቅዱስ እና እንደ ፈቃዱ ለቤተ ክርስቲያን በሚሰጣቸው ልዩ ልዩ የጸጋ ስጦታዎች አምናለሁ። እነዚህም የጸጋ ስጦታዎች ለአማኞች ሕንጸትና ለእግዚአብሔር ክብር ይውሉ ዘንድ በክርስቶስ ላመነ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ እንደ ወደደ የሚያድላቸውና የሚያለማምዳቸው እንደሆኑም አምናለሁ (ኤፌ. 4፥11-13)።

የነቢያትን አገልግሎት አስመልክቶ ግላዊ አቋሜ እነሆ!

1) በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን በስፋት የተጠቀሰው የነቢያት አገልግሎት፣ የእግዚአብሔርን አሳብ ማስተላለፊያ በመሆን እንዳገለገለና በማገልገልም ላይ እንደሆነ አምናለሁ። በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ቃሉን ወደ ሕዝቡ ከሚያመጣባቸው መንገዶች መካከል አንዱ የነቢያት አገልግሎት ነበር። የብሉይ ኪዳን ነቢያት ዋና ዓላማ የኪዳኑ ሕዝብ ከአምላኩ ጋር የገባውን ኪዳን እንዲያከብር ማድረግና ከኪዳኑም የተዛነፈ አካሄድን ባሳየ ጊዜ ከጠማማ መንገዱ እንዲመለስ ማሳሰብ ነበር። ነቢይነት በአዲስ ኪዳንም መንፈስ ቅዱስ ለቤተ ክርስቲያን ከሰጣቸው የጸጋ ስጦታዎች መካከል አንዱ ነው። ነቢይነትን ጨምሮ ሁሉም የመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ስጦታዎች ባለፉት ዘመናት ለአማኞች ከፍተኛ በረከት እንዳመጡ፣ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎትም ትልቅ ጉልበት በመሆን እንዳገለገሉና አሁንም በማገልገል ላይ እንዳሉ አምናለሁ። ለዚህ ክብሩን ልዑል እግዚአብሔር ይውሰድ!

2) የነቢያት አገልግሎት ዋነኛ ጥቅሙ (እንደ ሌሎቹ የጸጋ ስጦዎች) ቅዱሳንን ለማነጽ፣ ለማጽናናትና ለመምከር ነው (1ቆሮ 14፥3)። ይህም ማለት፣ ትንቢትን የሚናገር ሰው ጸጋውን የሚቀበለው ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽና ያላመኑ ሰዎች በንስሓ ወደ ጌታ ዘወር እንዲሉ ለመርዳት እንደሆነ አምናለሁ (1ቆሮ. 14፥24-25)!

3) የትንቢት መንፈስ የወንጌሉ ምስክር መሆን እንዳለበት አምናለሁ! በቅዱስ ቃሉ እንደተጻፈው የትንቢት መንፈስ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ነው (ራእይ 19፥10)። ስለዚህም፣ እውነተኛ ትንቢቶች ሁሉ ዋነኛ አንጽሮታቸውን (focus) ክርስቶስ ላይ በማድረግ ሕይወቱን፣ ስለ ሰው ልጆች ድነት በመስቀል መሞቱን፣ ትንሣኤውንና ዳግም ምጽአቱን የሚመሰክሩና አጠቃላይ ይዘታቸው ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ መሆን እንዳለበት በጽኑ አምናለሁ።

4) መጽሐፍ ቅዱስ የትንቢትና የነቢያት አገልግሎት ዋነኛ ዳኛና የሥልጣን ሁሉ ምንጭ እንደሆነ አምናለሁ! የእግዚአብሔር ቃል እስትንፋሰ-መለኮት እንደ መሆኑ ከሁሉ የጸና የትንቢት ቃል፣ የበላይ ባለሥልጣንና ዳኛ ነው (2ጴጥ. 1፥19)። ስለሆነም አማኝ ሁሉ የዛሬን ትንቢት መስማት ያለበት በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ላይ ቆሞ፣ ቃሉን ዋነኛ የመለኮታዊ ምሪት ምንጭና ዳኛ በማድረግ ነው የሚል የጸና እምነት አለኝ። የቅዱስ ቃሉን ትዕዛዝ ያላከበረና ለቃሉ ተገዢ ያልሆነ የትኛውም የነቢያት ልምምድና አስተምህሮ በጽኑ ሊሞገትና ሊጠየቅ ይገባዋል። ባልተገባ አካሄዳቸው የሚጸኑ ነቢያት ካሉም፣ መንጋውን ከጥፋት ለማዳን ቤተ ክርስቲያን በጽኑ መቃወምና የተጠና ርምጃ መውሰድ ይገባታል ብዬ አምናለሁ!

5) ትንቢትና ምልክቶች ሁሉ እንደ ቃሉ መመርመር እንዳለባቸው አጥብቄ አምናለሁ! ትንቢት ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ መሆኑን የማምነውን ያህል፣ በእግዚአብሔር ስም የተነገረ ትንቢት ሁሉ ከእግዚአብሔር መሆን አለመሆኑ መፈተንና መመርመር እንደሚኖርበት አምናለሁ። ይህንንም አስፈላጊ የሚያደርገው በየዘመናቱ ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት እየተነሡ ጤናማውን የወንጌል ትምህርትና የአማኞችን ሕይወት ስለሚያመሳቅሉ ጥንቃቄ ይደረግ ዘንድ ቅዱስ ቃሉ ስለሚያዝዝ ነው (1ዮሐ. 4፥1) ። የየትኛውም ትንቢት፣ ተአምር፣ ራእይ፣ ሕልም እና ትምህርት መለኪያው እንደ እግዚአብሔር ቃል ካልሆነ፣ ከአታላዩ ከዲያቢሎስ የመጣ ወይም ተናጋሪው ከራሱ ልብ ያመነጨው ሊሆን ስለሚችል (ኤር. 23፥16፤ ሕዝ. 13፥2) መጠንቀቅ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ። ቃሉ በግልጽ “ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳን እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ” እንደሚል (ማቴ. 24፥24) ስ ሁሉ፣ ሐሰተኞችም በዲያቢሎስ ኃይል ምልክቶችን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተጽፏል (ዘፀ. 7፥10፡11፤ 7፥20-22፤ ራእይ 16፥14፤ 13፥14፤ 19፥20)። ሌሎች የታሪክ ድርሳናትም በተለያዩ የእምነት ዘርፎች ተአምራዊ ምልክቶችና ትንቢቶች ስለ መኖራቸው ይጠቁማሉ። ለአብነት ያህል፣ በአፍሪካ ባህላዊ እምነቶች (African Traditional Religions) እና በጥንቆላ ልምምድ በሚደገፉ የአረማውያን ሃይማኖቶች በተለያየ ወቅት የተመዘገቡ በርካታ ተአምራዊ ምልክቶች እንዳሉ አስረጂዎች ተገኝተዋል። እነዚህ እምነቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ክርስትና መሠረት ያደረጉ ባለመሆናቸው ተአምራቱ በእግዚአብሔር ኃይል የተደረጉ እንዳልሆኑና ምንጫቸው ተቃራኒው ኃይል እንደሚሆን አይጠረጠርም። እነዚህን የሚመስሉ ሐሰተኛ ምልክቶችና ተአምራት፣ የተከፈተ በር ካገኙ ወደ ወንጌላውያኑ የማይገቡበት ምክንያት እንደማይኖር (ከላይ እንደ ተጠቀሰው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል) እና በመጨረሻው ዘመን ሐሰተኛ ነቢያትና ሐሰተኛ ምልክት አድራጊዎች በብዛት የሚነሡ በመሆናቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያሻ አምናለሁ!

6) በትንቢት ስም በወንጌላውያን ጎራ እየተካሄደ ያለውን ንግድና ርኩሰት ቅዱስ ቃሉ ላይ በመቆም በጥብቅ እቃወማለሁ! የትኛውም የጸጋ ስጦታ ቅዱሳንን ማገልገያ እንጂ ግላዊ ጥቅም ማግኛና ሃብት ማካበቻ አይደለም። እንደዚህ የሚያደርጉትም ወንጌሉን የጊዜያዊ ነዋይ ማትረፊያ ያደረጉ በመሆናቸው የእግዚአብሔርን ቃል ተመርኩዞ መቃወምና ከእነርሱ መራቅ ይገባል (1ጢሞ. 6፥4)።

7) ይፋ የወጡ የነቢያትና የሌሎች አገልጋዮች ሐሰተኛ ትንቢቶችና ሥነ ምግባራዊ ውድቀቶች ይፋዊ ንስሐና በተግባር የተገለጠ ተሐድሶ እንደሚፈልጉ አጥብቄ አምናለሁ። ከእግዚአብሔር ያልሰሙትን በመናገር ሕዝቡን ወደተሳሳተ መንገድ የመሩ፣ ያሸበሩና በስሙ ትንቢት የተናገሩበትን የእግዚአብሔርን ስም ያሰደቡ ነቢያት ጥፋተኝነታቸውን ሊሸፋፍኑ የሚችሉበት ምንም አይነት አግባብ ሊኖር አይገባም። በተመሳሳይ መልኩ በክርስቶስ የተገኘውን ሕይወት በማይወክል ሞራላዊ ውድቀት ውስጥ የተገኙና ይሄም ድካማቸው ይፋ የወጣ “አገልጋዮች”ም ይፋዊ ንስሓ ሊገቡና የጎዱትን ምዕመን ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባቸዋል። ከአገልግሎት በመታቀብም ራሳቸውን መመልከት፣ ቃሉን በጥልቀት በማጥናት አካሄዳቸውን መፈተሽና የንስሓን ፍሬ በሚገልጥ ሕይወት መመለስ መቻል ይኖርባቸዋል።

8) ከዚህ በተቃራኒ፣ የአንዳንድ “አገልጋዮች” የቃሉን መለኪያ ያላከበረ ሕይወት፣ የተዛነፈ አስተምህሮና ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች መሆን፣ ቃሉ “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” እንደሚል ከእግዚአብሔር ላለመሆናቸው አንዱ ምልክት እንደሆነ በመቁጠር በግልም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ደረጃ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብዬ አምናለሁ።

9) በመጨረሻም፣ እንደ አንድ የአዲስ ኪዳን አማኝነቴ ቃሉን በመመርኮዝ ከላይ ያሰፈርኳቸውን አቋሞቼን የሚቃረን የትኛውም ዐይነት የነቢያት እንቅስቃሴ እኔን የማይወክለኝና አጥብቄ የምቃወመው መሆኑን ወዳጆቼ ሁሉ እንዲያውቁልኝ አሳስባለሁ።

የእውነትን ቃል እንድናይ እግዚአብሔር ዐይናችንን ያብራ!

ጸጋው ከሁላችን ጋር ይሁን!


ምንጭ ፌስቡክ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.