ሰአቱ ደርሶ ይሆን? (ዮሐንስ መኮንን)

የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን ከ ስምንት ወራት በፊት ዓለማችንን በርዕዮተ ዓለም ለሁለት ስለሰነጠቃት የቀድሞዋ ታላቋ ሶቭየት ኅብረት ገናና መሪ ቭላድሚር ኤሊች ሌኒን ሲናገሩ ”በሀገራችን ቦንብ አጥምዶ ያለፈ መሪ” ሲሉ ባልተለመደ ሁኔታ ወቅሰውታል፡፡ ፑቲን ምክንያታቸውን ሲያስረዱ ”ሌኒን የተከለብን በዘር ላይ የተመሠረተ የክልሎች አወቃቀር ሀገራችንን ሰላም የራቃት ሉዓላዊነቷም አደጋ ላይ የወደቀ አድርጓታል፡፡” ሲሉ ወቅሰውታል፡፡ በክሬሚያ እና በሌሎችም የሩሲያ ግዛቶች የሚታየው ምስቅልቅል መንስኤው ሌኒን ያጠመደው ወቅቱን ጠብቆ የሚፈነዳ ፈንጂ (Time bomb) ነው ሲሉ አብራርተው ነበር፡፡

የኮሚኒስቶቹ የብሔር ፈንጂ የተቀበረው በሩሲያ ብቻ አይደለም፡፡ የሌኒንን እኩይ ምክር የሰሙ እኛን የመሰሉ ሀገራት ጭምር እንጂ፡፡ በየካቲት ወር 1968 ዓም በእጅ ተጽፎ የተሰራጨው የመሪዎቻችን ”መግለጫ” የተባለው ጽሑፍ በገጽ 8 ላይ ”የኅብረተሰብ መደብ መከፋፈል ለማጥፋት የተጨቋኙ መደብ አምባገነንነት እንደሚያስፈልግ ሁሉ የማይቀረው የብሔሮች መዋሀድ ሊገኝ የሚችለው መሸጋገሪያ በሆነው የብሔሮች ነጻነት ማለት የብሔሮች መገንጠል መብት ሙሉ በሙሉ መኖር ሲችል ብቻ ነው” የሚለውን የሌኒንን ርዕዮት በመጥቀስ የብሔሮችን ግንኙነት ለመወሰን አብነት በመውሰድ ይተነትናል፡፡

ባለፉት 25 ዓመታትም በሀገራችን የተዘራው የልዩነት ዘር እነሆ ፍሬ ይዞ ”የምሥራቹን” በአንዳንድ የሀገራችን አከባቢዎች እያየን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሶማሌ እና ኦሮሚያ የተፈናቀሉትን ወገኖቻችን ቁጥር ስናይ፣ ሰሞኑን ደግሞ በአንዳንድ ቦታዎች ዘር የለየ ዜጎችን ለሞት ለንብረት ቃጠሎና ለስደት የዳረገ ክስተት (በኦክቶበር 21-2017 ቢቢሲ የትግርኛው ዝግጅት እንደዘገበው) ስናስተውል የተቀበረው ወቅት ጠብቆ የሚፈነዳ ፈንጂ (Time bomb) ጊዜው ደርሶ ይሆን? እያልን እንሠጋለን፡፡ እንሳቀቃለን፡፡

ፑቲን ራሳቸው የኮምኒስት ሀሳብ አቀንቃኝ እና የኬጂቢ ሰላይ የነበሩ ሲሆን ”ያኔ የሠራነው ስህተት ነው፡፡ ያሰብናት ሩሲያም በምድር ላይ አልነበረችም” በማለት በጸጸት ተናዝዘዋል፡፡ ማንኛውም ሰው በወጣትነቱ አብዮተኛ፣ በአማካይ እድሜው ሚዛናዊ፣ በሽምግልናው ደግሞ መንፈሳዊ ዝንባሌ አለውና የፑቲን ጸጸት ተገቢ እና የሚጠበቅ ነው፡፡ ጥያቄው በሌኒን የብሔር ተቃርኖ ፍልስፍና የተጠመቁት የኛዎቹ የዛኔዎቹ አብዮተኞች የአሁኖቹ አረጋውያን መቼ ነው የሚጸጸቱት? የሚል ነው፡፡ ያኔ ያሰባቧት ኢትዮጵያ በምድር ላይ የለችምና! የተዘራው ዘር መራራ ፍሬ ሲያፈራ በስተርጅና እየታዘቡት ነው፡፡ ”ያኔ በወጣትነታችን ያሰብነው ስህተት ነበር፡፡ ሁላችንም በመደማመጥ የምንጓዝበት አዲስ መንገድ ያስፈልገናል” ብሎ ለመታረም ስንት ሰው መሞት፣ ምን ያህል ህዝብ መፈናቀል፣ ምን ያህልስ ንብረት መውደም ይኖርበት ይሆን?

መፍትሔው አንድ ነው፡፡ ሁላችንንም አሸናፊ የሚያደርግ እና መደሰላም መስክ የሚያሻግረንን ድልድይ ለመገንባት እጅ ለእጅ ለመያያዝ ምናልባትም የቀሩን ጊዜያት ብዙ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ አሁን እየታዘብነው እንዳለነው ከሆነ ፈንጂው በማንኛውም ሰአት ቢፈነዳ ከመሀከላችን ለወሬ ነጋሪ የሚተርፍ መኖሩን መተንበይ አይቻልም፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.