ጉራጌ ክልል የለውም ክልሉ ኢትዮጵያዊነት ነው

ለዳንኤል ብርሃኔ፦ አዎን እኛ ጉራጌ ኢትዮጵያውያን ፈሪዎች ነን

ፍርሃት ጥበብ ነው
ሃይልም የእግዚአብሔር ነው።

አዪ ዳንኤል! ዛሬም እዚያው ነህ! ለጉራጌው መቆርቆርህን ባደንቀውም በከንቱ እንዳትደክም ልንገርህ። ነቀምት ውስጥ ዋናውን መንገድ ይዘህ ብትሄድ አብዛኛው የንግድ ተቋማት የጉራጌ ብሔር ተወላጅ ኢትዮጵያዊ ኦሮሞዎች ናቸው። ጉራጌ ጠባቂው ፍቅር እና ፈጣሪው ነው። የመጠበቂያ ግንቡም ይኸው እምነቱ ነው። ቀዬውን ለቆ የትም ሀገሬ ነው ብሎ ኢትዮጵያዊነቱን ተማምኖ ለስራ የወላጆቹን ምርቃት ተቀብሎ ይወጣል፣ የትኛውም የኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ንብረት አፍርቶ ከህዝብ ጋር ይኖራል። ኢትዮጵያዊነት ጋሻ መከታው ነው፣ ፍቅር ማህተሙ ነው። አለኝ ብሎ አይታበይም አገኘሁ ብሎ በሀብቱ አይመካም፣ መመኪያው ፍቅር፣ እና ፈጣሪ ነው። ክብሩ ስራና ህዝብ ነው። ወዶና ተዋዶ የትም ይኖራል የትም ያድራል። ቂምና እና በቀል ቋንቋው ውሰጥ የለም፣ ስራ ክብሩ ፣ ድካም ግብሩ፣ ጥላቻ ጠላቱ ነው። የነቀምት ሰው ጉራጌን መግደል ቢፈልግ ማጥቃት ቢፈልግ በአንድ ሳይሆን በሺ ሊያስቆጥር ይችላል፣ ከፍቅር ውጪ ምንም አያግደውም፣ የመልስ ምትም እንደማያገኘው በደንብ ያውቃል። ግን አላደረገውም አያደርገውምም። ምክንያቱም ፍቅር ያሸንፋል።

ጉራጌ ብሔርተኛ አይደለም። በአጋጣሚ አንድ አይደለም ብዙ ጉራጌ በግርግር ቢሞት የብሔር ጥቃት ተነሳብኝ ብሎ ሊጮህ የሚችል ሳይሆን ነገርን ለናንተ ትቶ በደሉን ለእግዚአብሔር የሚነግር እንጂ። አንተ አንድ ጉራጌ አልክ እንጂ በሺዎች በመቶ ሺዎች ብትገሉብን መልሳችን አንድ ነው። መልሳችን ሀይል የእግዚአብሔር ነው ነው። ቢበዛ ለሀገር ሽማግሌዎቻችን፣ገዳይን እንዲረግሙ መንገር ነው። ጉራጌ ክልል(ገደብ) የለውም ክልሉ ኢትዮጵያዊነት ነው። እናንተ የሰራችሁለት ገደብ ሳይገድበው፣ በሄደበት ሁሉ በእሳት ንብረቱ ሲጋይ ሲፈናቀል ቀዬይን፣ ያሳደገኝን ህብረተሰብ አልለቅም ብሎ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በሰላም ከሰዉ ጋር አብሮ እየኖረ ነው። በአንድ ወቅት አንዱ ባለሀብት ለጉራጌ ልማት ምንም ሳትሰጥ እንዴት ለኦሮሚያ ይህን ያህል ገንዘብ ትሰጣለህ ስለው ያለኝን መቼም አልረሳውም። የጉራጌ ህዝብ ምን ስላደረገልኝ ነው የምሰጠው? ሀብት ያከማቸሁት ስራ የለመድኩት ያደግሁት ለዚህ የበቃሁት ኦሮሚያ ውስጥ ነው። እንደውም ብሔር በምርጫ ቢሆን ኖሮ እራሴን ኦሮሞ አደርግ ነበር ያለኝ። ጉራጌ ያሳደገውን ቀዬ የሚወድ ከማንም ጋር የሚዛመድ በፍቅርና በመተማመን ላይ ትልቅ እምነት ያለው ነው! የጉራጌ ህዝብ ከመግደል መሞት የሚመርጥ ነው። መግደል ከሀጢያትነቱ ባለፈ እጅግ የተወገዘ ተግባር ነው። ከመጉዳት መጎዳትን የሚመርጥ ነው፣ ባህልና አስተዳደጋችን ያስተማረን ይህንኑ ነው። ፈሪ ናችሁ በለን፣ አዎን ፈሪ ነን! ገሎ መፎከርን የምንጠየፍ ፈሪዎች ነን። ደም አፍሶ ከማጓራት የፈሰሰን የሰው ደም ላለማየት አይናችንን ከልለን የምናልፍ ፈሪዎች ነን! ፍርሃት ጥበብ ነው ወዳጄ! ፍርሃት ሀገርን አያፈርስም፣ ፍርሃት ፍቅርን አያጎድፍም። ባህሪ በዘር የሚወረስ ሳይሆን የአስተዳደግ ውጤት ነው። ህብረተሰቡ ፍርሃት እና ፍቅር ነው ያወረሰን፣ ያስተማረን፣ እናንተ የምትቀልዱበት የቋንቋችንን ዘዬ እና ቅላፄ ቀስ ብሎ ለሰማው እኮ ፍቅርና ርህራሄ የፈጠራት ቶን ነች። ጉራጌ ክልል የለውም፣ ገደብ አይወድም አያውቅም፣ ጊዜ ያመጣውን ነገር ማንም ላይ ሳያላክክ ፣ በብልሃት ነገሮችን የመወጣት አቅሙን ይጠቀማል እንጂ የጥላቻ መርዝ በመርጨት እሳትን በእሳት አያበርድም። በሀሳብ ልዩነት ያምናል፣ የሀሳብ ልዩነቶች የሚታይበት ንፁህ መነፅር አለችው፤ፍርሃት። የሃሳብ ልዩነቱን የሚዳኝበት ስርአት አለው፤ ሽምግልና። ስደት ፣መፈናቀል፣ ንብረት መውደም እና ሞት ለ26 አመት አብሮት የኖረ ብዙም የማይደንቀው ነው። አንተ ዛሬ ያሰብከው ለእኛ “ልብ ይስጣቸው” ብለን ከማለፍ ውጪ፣ ሃገራችንን ኢትዮጵያ ሁሌም ከጉራጌ ወላጆቻቸውን አፍ ጠፍቶ የማያቀውን ፣ “ፈጣሪ ሃገራችንን ይጠብቅ” ከማለት ውጪ ምንም አንልም። ምክንያቱም ወንድም ወንድሙን መግደል ጀግንነት የሚያሰኝ ከሆነ እኛ እድሜ ልክ ፈሪዎች እንባል እንጂ አናደርገውም። ጀግንነት ሲዘምን እኛ ጋ ታገኘዋለህ።

ብዙ ሳትደክም ልንገርህ አንድ ጉራጌ እስኪቀር ድረስ ብትጨፈጭፉን የመጨረሻው መልሳችን ወንድም ወንድሙን አይገልም ነው። ምክንያቱም ባህላችን አይፈቅድም፣ ምክንያቱም እምነታችን አይፈቅድም፣ ምክንያቱም ጉራጌ በፍቅር ያምናል፣ ጉራጌ በመተሳሰብ ያምናል፣ ምክንያቱም ጉራጌ ሃይል የእግዚአብሔር ነው ብሎ ያምናል። ምክንያቱም ጉራጌ ፈሪ ነው፣ ፍርሃት ጥበብ ነው።

ባይሆን መከራውን ኑሮውን ያከበደብን ፣ ያፈናቀለን የገበያ ማዕከላትን ያጋየብን ከ97 በኃላ ሁለንተናዊ ጥቃት እና ዘመቻውን እኛ ላይ እንዲያቆም ፀሃዩን መንግስትህን ጠይቅልን።

ልብ ይስጣችሁ!

ይህ የእኔ ብቻ ሃሳብ ሊመስልህ ይችላል፣ የሁላችንም ነው፣ ምክንያቱም የጉራጌነት መገለጫው አስተዳደግ እንጂ ደም አይደለም። ያደግነው በባህሉ ተኮትኩተን ስለሆነ የአመለካከታችን አንድነት ከአንድ ምንጭ ስለተቀዳ ነው!

በነገራችን ላይ ጉራጌ ብሔር በመወለድ እንጂ በደም ይወረሳል ብሎ አያምንም። ጉራጌ ሀገር የተወለደ ጉራጌ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። በፍቅር ያሳደገውን ህብረተሰብ የሚከዳ ልጅም ያሳደገውን ልጅ የሚከዳ አባትም ስለሌለ የትኛውም ብሔር ከተወለደበት ካደገበት አካባቢ አይፈናቀልም።

አትድከሙ፣ ጭንቅላታችሁን ይዛችሁ አትዙሩ

ተጠቀሙበት።
ጉራጌ እሳትን በእሳት የማጥፋት ልምድ የለውም።
ጉራጌና ገንዘብን ለልማት ትታችሁ ከፈለጋችሁ ሌላውን ለፖለቲካ ተጠቀሙበት።
ነገር ግን የወንድሞቻችን ደም እና ቁስል ለእኛ ክፉ ህመም ነው። ብትችሉ ኢትዮጵያዊነት ከደዌ መፈወሻ መድሃኒት እንደሆነ ለመቀበል ሞክሩ። ትኮረኩሙት ይሆን እንጂ አትገሉትም።
ኢትዮጵያዊነት ጉራጌ እና እባብ አፈር ልሰው ይነሳሉ እንጂ አይሞቱም።
ከረ የትሳከት!
ኢትዮጵያ ትቅደም!!!

በአበጀ ገንዘቤ (https://www.facebook.com/abejegenzebe)

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.