አገራችን ኢትዮጵያና የወቅቱ የክርስትና አቅጣጫ – “ወደ አንተ መልሰን” (ክፍል ፩)

Like | Comment | Share

“ማንኛውም መንግሥት ሥልጣኑና ኀላፊነቱ እስከምን ድረስ ነው? ማንኛውም መንግሥት ለሰላም፣ ለፍትሕና ለእኩልነት መቆም ሲገባው በተቃራኒው ጨቋኝና ኢፍትሐዊ ከሆነ፣ የቤተ ክርስቲያን ድምፅ ምን ሊሆን ይገባዋል? በኢትዮጵያ ለተከሰተው ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቀውስ የቤተ ክርስቲያን ምላሽ ምንድን ነው? በማስታረቅ ሂደት ውስጥ፣ እውነትና ምሕረት፤ ጽድቅና ፍትሕ መገናኝት አለባቸው ስንል ምን ማለታችን ነው?

በመጋቢ ግርማ በቀለ (/) ከቶሮንቶ

መግቢያ

የእግዚአብሔር ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ!

አገራችን ኢትዮጵያና የወቅቱ የክርስትና አቅጣጫ በየቤታችን የምንወያይባቸውና የምንጸልይባቸው ብርቱ ርእሰ ጉዳዮች ናቸው። “ምን ይበጃል?” የሚለው ጥያቄ የእያንዳንዳችንን ቤት አንኳኩቶአል፤ ብሔራዊ ጥያቄም ሆኗል። ለችግሮቻችን መንሥኤም ሆነ መፍትሔ በርካታ ፈርጀ ብዙ ምላሾች እየተሰጡ ናቸው። በዚህ አገራዊ ውይይት ውስጥ፣ “ክርስቶስን እንዳማከለ አማኝ ኀላፊነታችንና ድርሻችን ምንድን ነው?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ጥቂት ሐሳቦችን አቀርባለሁ። እንደ እግዚአብሔር ቃል መጋቢ፣ እይታዬ ወደ አንድ ጐን ብቻ ያዘመመ እንዳይሆን፣ የምችለውን ያህል ጥንቃቄ አድርጌአለሁ። ስለዚህ የዚህ መልእክት ወገንተኝነት፣ ከእግዚአብሔር መንግሥት የጽድቅ ሥራ ጋር ብቻ ነው። ዐላማውም ዕርቅ፣ ፈውስ፣ ሰላም፣ መልካም አስተዳደር፣ አንድነትና እድገት እንዲመጣ በሚደረገው ብሔራዊ ውይይት ውስጥ፣ ቤተ ክርስቲያን ተኣማኒነት ያለው የራሷን ትንቢታዊ ድምፅ እንድታሰማ በትሕትና ጥሪ ማቅረብ ነው።

የአገራችን ክርስትና አራት ዐበይት ተግዳሮቶችን መጋፈጥ ይኖርበታል። በመጀመሪያ እየደፈረሰ ያለው የቤተ ክርስቲያን ማንነት፣ ተልእኮና አንድነት ጥያቄ፤ ሁለተኛው ጐሣዊ ጽንፈኝነት፤ ሦስተኛው አስከፊ ድኽነት፤ በመጨረሻም ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት፣ በተለይም የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ጥያቄዎች። ይኽን ተግዳሮት በተመለከተ፣ ቤተ ክርስቲያን “አያገባትም፣ ገለልተኛ መሆን አለባት” ከሚለው ጀምሮ፣ ማንነቷና መልእክቷ ፖለቲካዊ ልብስ እንዲለብስ ያደረጉ አመለካካቶች ይሰማሉ። በዋነኛ ምሳሌነት የሚጠቀሰው፣ በቅርቡ፣ በጣም የማከበራቸው ቄስ ዶ/ር ቶለሳ ጉዲና፣ በየትኛውም ሙያዊ ትንታኔ ቀሊል ምላሽ የሌለውን ውስብስብና አስቸጋሪ የኢትዮጵያ ጎዳና፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የአጼ ኀይለሥላሴን ዘውዳዊ አገዛዝ በግፍ በማውረዱ ምክንያት፣ አምላክ ክብሩን ከምድሪቱ ላይ በማንሣቱ የመጣ የጥፋት መንገድ ነው የሚለው ድምዳሜ ነው። (ይህን በተመለከተ ራሱን የቻለ ትንታኔ በቅርቡ አቀርባለሁ)።

የክፍፍል ጽልመት ባጠላበት አገር፣ በሕዝበ ክርስቲያኑ መካከል የሚታየው የአመራር፣ መንፈሳዊ፣ ሞራላዊና ምግባራዊ ቀውሶች፣ የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮና መልእክት ተኣማኒነት ጥያቄ ውስጥ እየከተቱ ይገኛሉ። አገርን እያመሰ ያለው ችግር፣ ቤተ ክርስቲያንንም የሚያምስ ከሆነ፣ ቤተ ክርስቲያን የችግሩ አካል እንጂ፣ የችግሩ መፍትሔ ልትሆን በጭራሽ አትችልም። ከጌታ በአደራ የተቀበልነው የማስታረቅ፣ አገልግሎት እኛን ከከፋፈለን ሌሎችን ከእግዚአብሔር ጋር በክርስቶስ ታረቁ ብለን መመስከር እንዴት እንችላለን? ውድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ ኢትዮጵያ የጋራ አገራችን ከሆነች፣ በጋራ ለመወያየትና ችግሮቻችንን በጋራ ለመፍታት ቊርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል። “የእኔ አመለካከት ብቻ” ከሚል መከፋፈል፣ “ለአገር፣ ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ ምን ይጠቅማል?” ወደሚለው በአንድነት ላይ የተመሠረተ ምክክርና ውይይት ልንሄድ ይገባል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ጸለየው አንድነት እንጂ መከፋፈል ከቶ አይበጀንም።

መድኀኒታችን እንዳለው፣ “እርስ በእርሱ የተከፋፈለ መንግሥት ሁሉ ይወድቃል፤ እርስ በእርሱም የተከፋፈለ ከተማ ወይም ቤት አይጸናም።” (ማቴ. 12፥25)። ይህን ወቅታዊና ብርቱ የክርስቶስ ድምፅ ኢትዮጵያ፣ በተለይም ቤተ ክርስቲያን ከልብ ልትሰማው ይገባል። በአገራችን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሚቀርቡ ክርስቲያናዊ አስተያየቶች እንዴት ቢቃኙ ይሻላል? መቼስ የአገራችን ውስብስብ ችግር በአንድ ሰው ወይም ቡድን ብቻ፣ ሙሉ መፍትሔ ያገኛሉ ብሎ ማሰብ ተላላነት ነው። ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ እየተካሄደ ያለውን ክርስቲያናዊ ውይይት፣ ይበልጥ ጤናማና ውጤታማ ወደ ሆነ አዎንታዊ አቅጣጫ ለመውሰድ ትንሽ እገዛ ያደርጋል በሚል ተስፋ ያመንኩባቸውን ጥቂት ሐሳቦች እንደሚከተለው ሰንዝሬአለሁ።

 1. ቤተ ክርስቲያን ምን ጊዜም የእግዚአብሔርን ተልእኮ እንድታራምድ በራሱ በእግዚአብሔር የተመሠረተች መለኮታዊ አካል ናት። ተልእኮዋ እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የጀመረውን የድነት ሥራ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል በቃልና በተግባር ለዓለም ሁሉ ማብሰርና ከፍጻሜ ማድረስ ነው (ማቴ. 28፥19-20)። መልእክቷም የተሰቀለው፣ የሞተው፣ የተነሣው፣ አሁን በአብ ዘንድ የተቀመጠውና በክብር ዳግመኛ የሚመለሰው ክርስቶስ ብቻ ነው (1ቆሮ. 1፥23)። የውቅሯም እሴት መለኮታዊ ነው። ይህም ማለት ማንነቷና ተልእኮዋ የተመሠረተው በእግዚአብሔር ማንነትና ዐላማ ላይ ነው። ባለቤቷም፣ ተጠሪነቷም፣ ወገንተኝነቱም፣ ልሳኗም፣ የህልውናዋም እስትንፋስና ኀይል “የገሃነም ደጆች አይችሏትም” ያለው ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። በመንግሥትም፣ በተቃዋሚም፣ በማኅበራዊ ድርጅትም ሆነ በግለሰብ ልትመካ አይገባትም። ምስባኳም ሆነ ዐውደ ምሕረቷ ከእነዚህ ኀይላት አጀንዳና ተጽእኖ የጸዳ መሆን አለበት። ቤተ ክርስቲያን ፖለቲካዊ ዝመት ያልደረበ የእርቅና የሰላም መንገድ መሆን የምትችለው፣ ይህንን ተልእኳዊ ማነንት በእውነት ስትኖረው ብቻ ነው። እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር በገባው ቃል ኪዳን መሠረት፣ በቤዛዊ የድነት ሥራ ውስጥ የእስራኤል ሕዝብ የመሲሑ ዘር ተሸካሚ እንዲሆኑ ከግብፅ የባርነት ቤት ነጻ አወጣቸው (ዘጸ. 2፥24)። ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ የመታሰባቸውና ከፍትሕ የለሽ፣ ጨቋኝና ጨካኝ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘረኛ አገዛዝ ዐርነት የማግኘታቸው ዋነኛ ምክንያት፣ ለእግዚአብሔር የተለየ ሕዝብ በመሆን በጨለማ ላለው ሕዝብ ብርሃን ለመሆን ነበር። ወደ ተስፋዪቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት በሲና ተራራ ላይም ዐሥርቱ ትእዛዛት የተሰጧቸው፣ የዐርነታቸው ማንነትና ተልእኳቸው የማይነጣጠሉ መሆኑንን በአጽንዖት ለማሳወቅ ነበር። በተመሳሳይ መልኩ፣ ይኸው ማንነትና ተልእኮ የአዲሱ ኪዳን ማኅበረሰብም መሆኑን ሐዋርያት አረጋግጠዋል። ቃሉ እንደሚል፣ “እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁ የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ” (1ጴጥ. 2፥9)። ማንነቱና ተልእኮው የገባው ትውልድ ከእግዚአብሔርና ከሰው ጋር ያለው ግንኙነት ለአንዴና ለዘላላም ተቀይሯል። እግዚአብሔርን፣ ራሱንና ዓለምን የሚያይበት እይታ ሥር ነቀል በሆነ መልኩ ተለውጧል! የአዲስ ኪዳንም መልእክት ይኸው ነው። ከትንሣኤው በኋላ፣ ክርስቶስም የደቀ መዛሙርቱን ዐይኖች የከፈተበት ዐቢይ ምክንያት ይኸው ብቸኛ ተልእኮ ነው (ሉቃ. 24፥44-48)።
 2. የሰው ልጅ ዋነኛ፣ ግለሰባዊም ሆነ ማኅበራዊ ችግር ሥሩ አለመታዘዝና ዐመፅ የወለደው ኀጢአት ነው። በኦሪት ዘፍጥረት ላይ እንደምናየው፣ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ” (1፥31)። ይህን “እጅግ መልካምነት” ያበላሸው፣ የኀጢአት ወደ ዓለም መግባት ነው። ኀጢአት ሦስት የግንኙነት ስብራትና ቀውሶች አምጥቷል፤ በእግዚአብሔርና በሰው፣ በሰውና በሰው (አስተሳሰብን፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የግንኙነት መዋቅሮችን አቃውሷል) እንዲሁም በመጨረሻ በሰውና በተፈጥሮ መካካል።
  የክርስቶስ ተልእኮ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አይደለም፤ ሰው ያጣውን የእግዚአብሔርን ክብር ቤዛ ሆኖ መመለስ እንጂ! ከዘፍጥረት እስከ ራእየ ዮሐንስ የምንመለከተው ይህንኑ የታሪክ ውቅር ነው። ስለዚህ ወንጌል፣ ከፍ ሲል የተጠቀሱትን የግንኙነት ስብራትና ቀውሶች ክርስቶስ በሥጋ በመወለድ (ትስብእት በመሆን)፣ በመስቀል ሞቱና በትንሣኤው የመፈወሳቸው የምሥራቹ ነው። (ሮሜ 1፥4)። የሰው ልጅ ዋነኛ ችግር ኀጢአት ነው፤ መፍትሔውም ምድራዊ አይደለም። ወሳኙና ምትክ የሌለውም መፍትሔ ወንጌል ብቻ ነው። እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ክርስቶስን በብቸኛ የመጨረሻ መፍትሔነት ለዓለም የሰጠው፣ የክፋት ሁሉ ጉሮኖ የሆነውን የሰው ልጅ ልብ እንዲያው በጸጋው አዲስ ለማድረግ ነው። ስብከታችንም ይኸው የመስቀሉ ቤዛዊ ሥራ ብቻ ነው።
 3. በክርስቶስ ሥራ የቤተ ክርስቲያን ዜግነነት በቅድሚያ ሰማያዊ ቢሆንም፣ በዚች ምድር እስካለች ድረስ ማኅበራዊ ማንነትም (sociological entity) አላት። እግዚአብሔር በፍጥረት መግቦቱ (providence) ሰውን ሁሉ ያኖራል። ፀሓይና ጨረቃ፥ ክረምትና በጋ ለሰው ሁሉ በነጻ የተሰጡ የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው። ሰው ከፍጥረቱ አምላካዊ አምሳል የታተመበት በመሆኑ፣ በእግዚአብሔር ቸርነት ይኖራል። “እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሓይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኀጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና” (ማቴ. 5፥45)። ሰው ባይገነዘብም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስኬት የእግዚአብሔር ሉዓላዊ የቸርነት መግቦት ነው። ይህም የክርስትና አንጋፋ እውነት ነው። የአሁኑ ዓለም የክርስትና ኑሮ በተፈጸመና ሊፈጸም ባለ (already, but not yet) የጊዜ ውጥረት መካከል የሚኖር የሰልፍ ኑሮ ነው። በዚህ መልኩ የክርስትና መልእክት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አንድምታዎች ወይም ክትለቶች (implications) አሉት። ምድራዊው ኑሮአችን ከቶ ላይነጠል ከምድራዊ ዜግነታችን እንዲሁም የሕይወት ትግልና ተስፋ ጋር ተጋምዷል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሆነው ነገር ሌሎችን በሚመለከትበት መጠንና ደረጃ እኛንም በደጉም በክፉም ይመለከታል። ለፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶች ባይተዋር ልንሆን አንችልም። ተልእኮአችን ኀጢአት ከበዳይ ክፉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገዛዞች፣ አስተሳሰቦችና ባህሎችና ጋር እንደ ድርና ማግ የተጠላላፈ መሆኑን ግምት ውስጥ ያስገባ ሊሆን ይገባዋል። በተጨማሪም ከየትኛውም እኲይ ማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ጀርባ የክፋት ኀይሎች መኖራቸውንም ልብ ልንል ይገባል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለክፋት ኀይሎች የተሰጠው መጠሪያ፣ “ክፉ፣ ነፍሰ ገዳይ፣ የሐሰት አባት፣ መንፈሳዊ ዐይን አሳዋሪ፣ የክርስቶስ ጠላት” የሚል ሲሆን፣ ሰይጣን በሥራ ላይ መሆኑንም ምን ጊዜም ልንዘነጋ አይገባም። መጋደላችን ቅዱስ ቃሉ እንደሚል፣ “ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፤ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ” (ኤፌ. 6፥12)።
  ክርስቲያናዊ ሕይወት ምሉእ ሕይወት ነው፤ ከፊሉ ምድራዊ፣ ከፊሉ ሰማያዊ ወይም ከፊሉ ዓለማዊ. ከፊሉ ጽድቃዊ በሚል አይከፋፈልም። ማንኛውም ሕይወት ለእግዚአብሔር ክብር መኖር አለበት። ከዚህ አንጻር፣ “አገራችን በሰማይ ነው፤ በምድር መጻተኞች ነን” የሚለው አባባል በአንድ ጐኑ ብቻ የተወጠረና የተፋለሰ የማንነት ቀውስ ነው። ተልእኮአችን ብሔራዊ ዕርቅና ተሐድሶ እንዲመጣ በሚደረገው ውይይት ውስጥ ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ ተሳታፊነትን ይጨምራል። “አእምሮንም ሁሉ እየማረክን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እናደርጋለን” (2ቆሮ. 10፥5)። በሁለንተናዊ የሕይወት ፈርጅ፤ በትውልድ ላይ የጽድቅ ተጽእኖ ማለት ይህ ይመስለኛል። ክርስቲያን ሆንን ማለት አገራዊ ጒዳይ አይመለከተንም ማለት አይደለም። ይልቁንም አምላካዊ ተልእኮ የተቀበለ አማራጭ ማኅበረሰብ የመሆናችን ተኣማኒነት የሚለካው ለጨለመውና ጣዕም ላጣው ዓለም ብርሃንና ጨው በሆንበት መጠን ነው። ዓለምን በሕይወት ምስክርነትና በቃል በጽድቅ መኮነን ማለት፣ ኀጢአትን ኀጢአት፣ ግፍን ግፍ፣ በደልን በደል ማለት መቻል ነው።
 4. ቤተ ክርስቲያን፣ በምድር ላይ የእግዚአብሔር መንግሥት ወኪልና ትንቢታዊ ድምፅ ናት። ይህ ድምፅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለው ወይም ከዐውድ ተቦጭቀው የወጡ ጥቅሶችን በማስረጃነት በማቅረብ በማይጨበጥና ፈጽሞ እውን በማይሆን ተስፋ የተመሠረተው “የሀብትና የብልጽግና ትምህርት” የሚያስተምረው “የትንቢት አገልግሎት” አይደለም። የወንጌል አማኞች አንደኛው መንፈሳዊ ቀውስ፣ የቃለ እግዚአብሔርን መካከለኛነት ወደ ጐን ያሸሹ አስተምህሮአዊ ተፋልሶዎችና ድንበር ዘለል መንፈሳዊ ልምምዶች የወለዱት የተኣማኒነት ጥያቄ ነው። ትንቢታዊ ድምፅ ማለት ባጭሩ “የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶች ሁሉ ጌታ ለሆነው ለልዑል እግዚአብሔር ጽድቅ ልሳን መሆን ማለት ነው። “መንግሥትህ  ትምጣ” (ማቴ 6፥10) ማለት ይኸው ነው፤ በኀጢአት በተለወሰው የሰው ሁለንተናዊ የሕይወት ፈርጆች ሁሉ ውስጥ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ሕይወት የተገለጠውን፣ የእግዚአብሔርን መንግሥታዊ እሴት ወይም ፋይዳ ማስፋት ነው። እግዚአብሔር በሉዓላዊነቱ፣ “ዙፋኑን በሰማይ አጽንቶአል፤ መንግሥቱም ሁሉን ትገዛለች” (መዝ 103÷19)። የወንጌል ብርሃን በልቡ ላይ የበራ ሰው እግዚአብሔርን፣ የገዛ ራሱን፣ ጐረቤቱንና ምድራዊ ዜግነቱን የሚያይበት እይታው ለአንዴና ለዘላለሙ ተቀይሯል! በብሉይ ኪዳን፣ ለእስራኤል የተሰጣት ሥነ-ምግባራዊ/ሞራላዊ ሕግ፣ ለሐዲስ ኪዳኑም መሲሐዊ ማኅበረሰብ የአሰተሳሰብ እሴት መሠረት መሆኑን በጽናት ልናስተውለው ይገባል። እነዚህ ሥነ ምግባራዊ ሕግጋት በሐዲስ ኪዳኗ መሲሐዊ ማኅበረሰብ ተፈጻሚነት የለውም የምንል ከሆነ ትልቅ ስሕተት እንፈጽማለን። የሥነ ምግባር መርሖዎች (norms) በየትኛውም የታሪክ ዘመን እውን የሚሆኑ የአምላክ ባሕርዮታዊ መሠረት ናቸውና። አምላክ አይለወጥም ስንል ባሕርዮቱ አይቀያየርም ማለታችን ነው። አምላክ አለመቀያየሩ ደግሞ ምግባራዊ ሕግጋትን የማይነቀሱ የማይገሠሡ ነባራዊ መሠረት ያደርጋቸዋል። በግል ደረጃ ፍትሕ ሲጓደልብን፣ ስንበደልና ግፍ ሲደርስብን እንደ ነቢያት “የፍትሕ አምላከ የት ነው ያለኸው!’ ብለን መጽሐፍ ቅዱስን ጠቅሰን፣ ሰበአዊ መብቶችን ሞግተን ጩኸት እያሰማን፣ ለጐረቤታችን ወይም በስፋት ያየነው እንደሆነ በአገር ደረጃ ላለ ተመሳሳይ ጩኸት ባይተዋር (indifferent) መሆን ትልቅ ግብዝነት ነው።
 5. ቤተ ክርስቲያን በተፈጸመና ሊፈጸም ባለ (already, but not yet) የጊዜ ውጥረት ውስጥ ብትገኝም፣ የተሻለ የእርቅ፣ የሰላምና የፍትሕ አማራጭ ምልክት (sign) ማኅበረሰብ ናት። በዚህ የጊዜ ውጥረት መካከል የሚኖረው የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ ያለበት መሆኑን ልብ ልንል ይገባል። ሐዋርያው እንደሚል፣ “… በሰው እጅ ያልተሠራ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የሆነ ዘላለማዊ ቤት በሰማይ እንዳለን እናውቃለን … በዚህ ድንኳን እስካለን ድረስ [ሕይወት] ከብዶን እንቃትታለን…” (2ቆሮ. 5፥4)። የምንጠብቀው መንግሥት አለን፤ ፍጹም ፍትሕ፣ ሰላም፣ ደስታና ዕረፍት፣ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት እውን የሚሆኑ ተስፋዎች ናቸው። ከዚህ አንጻር፣ በምድር ላይ ፍጹም ፍትሕ፣ ሰላም፣ ደስታና ዕረፍት የሚያመጣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዐት የለም—አንጻራዊና በየጊዜው የሚሻሻል እንጂ። ቤተ ክርስቲያን በእነዚህ የጊዜ ውጥረቶች መካካል ያለች፣ ተስፋ ላጣው የዓለም እውነተኛ ተስፋ ናት። ጌታ እንዳለው፣“እነሆ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና”። (ሉቃ. 17፥21)። በእርግጥ አማኞችን የሚገዛቸው ይኸው በውስጣቸው ያለው የእግዚአብሔር መንግሥት ከሆነ፣ ኀጢአት፣ ሞትና ሰይጣን የተሸነፉበት፤ ይልቁንም ፍጹም ፍትሕ፣ ሰላም፣ ደስታና ዕረፍት የሰፈነበትና ጌታ በወሰነው ቀንና ሰዓት የሚያመጣው ቡሩክ መንግሥት አምባሳደሮች መሆናቸው የግድ ነው።
 6. የክርስትና ዘላለማዊ ዋነኛ እውነት፣ የሰው ሁሉ ክቡርነትና የእኩልነት መሠረት በእግዚአብሔር መልክ መፈጠሩ ነው። “እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው” (ዘፍ. 1፥26-27)። ስለዚህ የሰው የክቡርነት ዋጋ በማኅበራዊ፣ ጐሣዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሥሪት በፈጠረው እሴት መለካት የለበትም። ማንንም ሰው ከትውልድ አገሩ፣ ከቈዳው ቀለም፣ ከብሔሩና ከጐሣው፣ ከቋንቋውና ከባህሉ የተነሣ አናሳና ገሚሰ ሰው አድርጎ መቊጠርና መበደል፣ በሰው ማንነት ላይ የታተመውን የመለኮት አምሳል መግፋት ወይም ማክፋፋት ነው። ጐሣዊ ጽንፈኝነትና ሌላውን ወገን አግላይነት ፈጽሞውኑ እግዚአብሔራዊ አይደሉም። እንዲያውም አምላክ የሚጸየፈው ግብር ነው። የብሔር ማንነት “ለእኔ ወይም የእኔ ብቻ” በሚል ንፉግነት ሲከር የአገርም ሆነ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ይናጋል። አንድ ብሔር፣ ከእርሱ በወጡና የመራር ጐሠኝነት እስረኛ በሆኑ አክራሪ ግለሰቦች፣ የፖለቲካ መሪዎችና ፓርቲዎች ዐይን በጅምላው ሊታይ አይገባም። ይልቁንም ይህን ቂምና መራራ ዘር መንቀል ያስፈልጋል።
 7. ከመስቀሉ ሥራ የተነሣ የክርስቶስ ማኅበረሰብ መታወቂያውም ሆነ ውቅሩ ዘር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ መደብ ወይም ፖለቲካዊ ርእዮተ ዓለም አይደለም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔርና በሰው፣ በሰውና በሰው መካካል ያለውን የጥል ግድግዳ ለአንዴና ለዘላላም አፍርሷል። እርሱ ሰላማችን ነው። ልክ እንደዚሁ፣ እርሱ በእርግጥ ጌታዋ የሆነላት ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ጐሣዊ እንዲሁም ሃይማኖታዊ ጽንፈቶች ለምትታመሰው ዓለም አስታራቂና ፈውስ ናት። መስቀሉ ድልድይ ነው። ቤተ ክርስቲያንም ሰዎች ባፈረሷቸው ግንኙነቶች መካከል እውነተኛ አማራጭ ድልድይ ልትሆን ተጠርታለች። አግላይነት፣ ተወጋጋጅነትና ጽንፈኝነት በነገሠበት በዚህ ዓለም፣ “ልዩ የእግዚአብሔር ሕዝብ” መሆን ምን ማለት እንደሆነ ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል (1ጴጥ. 2፥9)። በምድር ላይ ካሉ ማኅበረሰቦች ሁሉ፣ የክርስቶሰን ልዩ የሚያደርገው አዲሱ ማንነት ነው። የዚህ ማኅበረሰብ ወገንተኝነት ከእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅ ሥራ ጋር ብቻ ነው—የእውነተኛ ፍትሕና ምሕረት መገኛ አድራሻ የእግዚአብሔር ሕዝብ ነው። አማኙ ማኅበረሰብ ውበቱ ልዩነቱ ነው፤ ለእግዚአብሔር ለራሱ የተለየ ሕዝብ በሆነበት መጠን ያህል ብቻ ነው ለሌላው ሕዝብ የእርቀና ሰላም አማራጭ የሚሆነው። በእርግጥ ልዩ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከሆንን፣ የሚገዛንም ዋናው እሴት ደግሞ ከሕዝብ፣ ከነገድና ከቋንቋ የተዋጀንበት ማንነት ከሆነ፣ እርስ በእርስም ሆነ ሌሎችን በብሔርተኝነት መነጽር ልንመለከት አንችልም (ራእ. 5፥8-10)።
 8. ክርስቶስ የአገልግሎቱ መጀመሪያ ያደረገው ወንጌል ለድኾች (የነፍስም፣ የሥጋም) የምሥራች መሆኑን በማብሰር ነበር። “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድኾች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል” (ሉቃ. 4፥17-19)። በኢትዮጵያ አብዛኛው ሕዝብ ድኻ ነው፤ ቤተ ክርስቲያንም ለድኾች ጩኸት ግድ የሚለው ክርስቲያናዊ ተልእኮ ያስፈልጋታል። በአገራቸን በተለያዩ ግዛቶች ስላለው የልማት፣ የዐቅም ግንባታና ድኽነትን የመፋለም እንቅስቃሴ እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባል። ይሁን እንጂ ከድኽነት ጋር ያለን ፍልሚያ ተጀመረ እንጂ አላለቀም። ድኽነት እንዲህ በሚሳለቅብን ሰዓት፣ የተሻለ ኑሮ ለመፈለግ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው በባዕድ አገር በሚንከራተቱ ወገኖች ላይ ዐመፅ በትሩን አሳርፏል። ድኽነትና ረሀብ በተነሣ ቊጥር በምሳሌነት የምትጠቀስበትን የታሪክ መልክ የመለወጥ አደራ በእኛ ላይ ወድቋል። አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ለምናየው ድኽነት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥሪቶቻችን ተጠያቂዎች ናቸው፤ የእርስ በእርስ ጦርነት (በቅርቡ ከኤርትራ ጋር የነበረንን ጦርነት ያስታውሷል) እንዲሁም ድርቅና ረሀብ ተጠያቂዎች ናቸው (እርግጥ ምንጫቸው ሰውም ተፈጥሮም ነው)። እነዚህ ሁሉ የኢትዮጵያ መጥፎ ገጽታዎች ናቸው – መለወጥም ይገባቸዋል። ከእነዚህ በተጨማሪ መንግሥታዊና ከመንግሥት ዐቅም ጋር የማይተናነሱ፣ አገር ውስጥ ያሉና ድንበር ዘለል ኮርፖሬሽኖች የሚያራምዷቸው ድኻን አግላይና በዳይ የሆኑ ፍትሕ የጐደላቸው ኢኮኖሚያዊ ርዕዮተ ዓለሞች፣ የችግራችንን ጫና አክብደውታል። በጥቅሉ ሲታይ የዓለም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ውቅር ከሁለት ተከፍሏል – የበለጸጉ አገሮችና ድኻ አገሮች በሚል። ድኾች ይበልጥ ድኻ እየሆኑ ባንጻሩም ብልጡጐች ይበልጥ ብልጡግ እየሆኑ መጥተዋል። ይህም ማኅበራዊ ውቅር በአገራችን በግልጥ ይታያል። አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዓለም ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትሩፋት ተጠቃሚ አልሆነም። ዓለም ይበልጥ እያነሰች ከዚህም የተነሣ ሕዝቦች ይበልጥ እየተዛመዱ ቢመጡም፣ በሚሊዮኖች የሚቈጠሩ ኢትዮጵያውያን ሕልም ገና እውን አልሆነም። እናም የድኾች ጒዳይ የአገር አቀፋዊው ውይይት ዐቢይ ርእሰ ጒዳይ መሆን አለበት። እንደ ክርስቲያን መልሳችንና አማራጮቻችን ምንድን ናቸው? መቼም በጥቅሉ ሲታይ፣ የድኽነት መንሥኤም መፍትሔም ከአንድ መንግሥት አወቃቀርና ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ልብ ልንል ይገባል። በድጋሚ ልብ እንበል፣ የሰዎች ሁሉ ክቡርነትና እኩልነት መሠረት፣ በእግዚአብሔር መልክ መፈጠራቸው ነው። ሰውን፣ በተለይም በዕውቀትና በሥልጣኔ ወደ ኋላ የቀሩትን ሕፃናትን እና አረጋውያን፣ ለድኽነት አሳልፎ የሚሰጥ አስከፊና በዳይ የሆነ ማንኛውም ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲ ከዚህ እውነት ጋር ይቃረናል። የአንድ መንግሥት እውነተኛ ልማትና እድገት መለኪያው፣ ያለአድሎ ዜጐቹን በሙሉ የምድሪቱ በረከት እኩል ተካፋይ ማድረግ መቻሉ ወይም ያለመቻሉ ነው። ቤተ ክርስቲያን የድኾችና በኢ-ፍትሐዊነት የተበደሉ ሰዎች ጩኸት በጽድቅ መፍትሔ እንዲያገኝ የምታደርገው ጥረት መመሥረት ያለበት ዘመን በማይሽረው የሰው ልጅ ሁሉ ክቡርነትና እኩልነት ላይ ሊሆን ይገባዋል። የዚህ ጥረት እሴት፣ ቤተ ክርስቲያንን ከክፉ መዋቅሮችና አሠራሮች ጋር እንድትጋጭ ማደረጉ አይቀርም። ቢሆንም፣ ጥሪዋ ለጽድቅና ለላቀው ሰማያዊ ዜግነት እሴት መኖር ነው።
 9. ለአመራር ቀውስ እግዚአብሔር በመፍትሔነት ለሕዝቡ በስጦታነት የሚሰጠው እንደ ልቡ እና እንደ አሳቡ የሚያገለግሉ መሪዎችን ነው። በኀጢአት ቃል ኪዳናቸውን በማፍረሳቸው ምክንያት ወደ ባቢሎን በግዞት ከመወሰዳቸው በፊት እግዚአብሔር ለሕዝቡ አስቀድሞ የገባላቸው የተስፋ ቃል፣“እንደልቤም (የሆኑ) በግ ጠባቂዎችን (እረኞችን) እሰጣችኋለሁ፥ በዕውቀትና በማስተዋልም ይጠብቁአችኋል” የሚል ነበር። (ኤር. 3፥15)። ስለዚህ መሪ ስጦታ ነው፤ የአመራሩ ስኬት ደግሞ መሪው በእግዚአብሔር ፊት በሚኖረው የጽድቅ ኑሮና መሰጠት ይወሰናል። እግዚአብሔር የሀልዎቱ መተላለፊያ ያደረጋቸው ባሮች የትውልድ ስጦታ ናችው። ኢትዮጵያ አሁን ላለውም ሆነ ለወደፊት ትውልድ የሚያስቡ ባለራእይ አገልጋይ መሪዎች ያስፈልጓታል። ለራሳቸው ግለኛ አጀንዳ የማይኖሩ፣ ለገዛ ወገኖቻቸው ጥቅምን ብቻ ሳይሆን ለመላው ሕዝብ፣ በተለይም ለድኾች መብትና ጥቅም፣ እንዲሁም ለሚልቀው አገራዊና ሁለንተናዊ ፈውስ የሚጋደሉ መሪዎች ያስፈልጓታል። እውነት፣ ጽድቅ፣ ፍትሕና ምሕረት የወንበራቸው መሠረት የሆነ አገር መሪዎች፣ ሕግ አውጭና አስከባሪዎች፣ ዳኞች፣ ኀይላትና ሥልጣናት፣ ወታደሮች፣ አሠሪዎች፣ ባለሙያዎች፣ ባለ ሀብቶች፣ ነጋዴዎች ወዘተ ያስፈልጓታል። ከእነርሱ የተሻሉ መሪዎች ማፍራት ረሀባቸውና ትጋታቸው የሆነ፤ በተሰጣቸው ዘመን ትውልዱንና እግዚአብሔርን ካገለገሉ በኋላ፣ የተሰጣቸውን ኀላፊነት፣ በሕዝብ ለሚመረጡና ለዐደራ የሚበቁ መሪዎች በሰላምና በክብር ለማስረከብ አፍቃሬ ሥልጣን ወይም ወገንተኝነት እንቅፋት የማይሆንባቸው ያስፈልጉናል።
 10. ቅዱስ ቃሉ እንደሚያስተምረው፣ መንግሥት “ለመልካም ነገር የሕዝብ አገልጋይ” ነው (ሮሜ 13፥4)። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን፣ የየትኛውንም ዐይነት መንግሥት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የአስተዳደር መርሖና ውቅር ተኣማኒነት መለካት ያለባት በዚህ እውነት ነው። መንግሥታት ዕውቅና ሰጡም አልሰጡም፣ ለመልካም አስተዳደር የእግዚአብሔር አገልጋዮች ብቻ ሳይሆኑ፣ የሥልጣናቸው ምንጭ ራሱ ሉዓላዊው እግዚአብሔር ነው። በዚህ አንጻር የአገር መሪዎች የሥልጣን ሁሉ ባለቤት የሆነውን እግዚአብሔርን በመፍራት በፍትሕ፣ በጥበብና በማስተዋል እንዲያስተዳድሩ ቤተ ክርስቲያን መማለድና መምከር ይኖርባታል። መቼም ቢሆን ፈሪሓ እግዚአብሔር ያለው፣ በጽድቅ፣ በፍትሕና ምሕረት ላይ የተመሠረተ አመራር ለብሔራዊ አንድነትም ሆነ ለጋራ ብልጽግና ወሳኝ መሆኑን ማሳስብ ያስፈልጋል። የአገራችንም መንግሥት የመልካም አስተዳደር መሠረታዊ እሴት ዘብ መሆን ይገባዋል። በተለይም ለድኾችና ከዕውቀት ማነስ የተነሣ ለራሳቸው መብት መቆም ለማይችሉ፣ ከሀገሪቱና ከዓለም እድገትና ብልጽግና ክልል መስመር ውጭ ያሉ ዜጐች ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል (ኤር. 21፥12፤ ያዕ. 1፥27)
 11. ነፍስን መግደል – በተለይም ንጹሕን – የእግዚአብሔርን አምሳያ ማፍረስ ነው (ዘጸ. 20፥13)። ክርስቶስ ጥላቻን፣ ከነፍሰ ገዳይነት ጋር አቆራኝቶታል (ማቴ. 5፥20-21፤ 1ዮሐ. 3፥15-17)። አሁን አገሪቱ ካለችበት የሰላም መደፍረስና ውጥረት ለመውጣት፣ ከገዢው ፓርቲም ፣ ከሕዝብም፣ ከተቃዋሚም ቡድንም የሚሰነዘር ዐመፅ አያዋጣም። የአሁኑ ውጥረት የቆየ ጐሣዊና ሃይማኖታዊ ጽልመት በላዩ አንዣብቧል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ከ80 በላይ ቋንቋዎች በሚነገሩበት አገር፣ ዕውቀትን ብስለትንና መከባበርን መሠረት ያደረገ “መቻቻል” ዐይነተኛ መፍትሔ እንደሆነ ለመግለጽ እወዳለሁ። የዚህን “መቻቻል” ጤንነት መጠበቅ ልዩ አጽንዖት ሊሰጠው ይገባል። ይህንን ተቻችሎ የመኖር አንድነት፣ ሊያናጋ የሚችል ጐሣዊ፣ ሃይማኖታዊም ሆነ ርዕዮተ-ዓለማዊ ጽንፈኝነት በር እንዳይከፈትለት ከምንጊዜውም በላይ ልንጠነቀቅ ይገባል። ጽንፈኝነት ደምኖ ከዘነበ፣ ሕዝብና አገር ይተራመሳል፤ የአገሪቱን አንድነት ለማይወዱ፣ ጠላት አገሮች በር ይከፍታል። ዩጐዝላቪያን፣ ሩዋንዳን፣ ኮንጐን (“የአፍሪካ ዓለም ጦርነት” በሚባል የሚታወቀው ሁለተኛው ጦርነት)፣ ሰሜናዊ አየርላንድንና ሌሎች በርካታ አገሮችን በደም ያጠበ ጐሳዊና ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት፣ የቅርብ ጊዜ ትዝታ መሆናቸውን ልብ ልንል ይገባል።
  በድጋሚ ላሳስብ፤ እግዚአብሔር መንግሥታትን የሚያስቀምጠው፣ የጽድቅ፣ የፍትሕ፣ የፍርድና የምሕረት አገዛዝ አስፈጻሚ እንዲሆኑለት ነው። የፍትሐዊ አገዛዛቸውም ተኣማኒነት መለኪያው ይኸው እውነት ነው። ቃሉ እንደሚል፣“ነገሥታት በእኔ ይነግሣሉ፤ ገዦችም ትክክል የሆነውን ሕግ ይደነግጋሉ፤ መሳፍንት በእኔ ይገዛሉ፤ በምድር ላይ የሚገዙ መኳንንትም ሁሉ በእኔ ያስተዳድራሉ” (ምሳ. 8፥15-16፤ ሮሜ 13፥1-7)። በታሪክ፣ “ዜግነታችን በሰማይ ነው”፤ ወይም “ማንኛውም ሰው በሥልጣን ላሉት ሹማምት መገዛት ይገባዋል” በሚሉና በሌሎችም ከዐውዳቸው ውጭና ከቅዱሳት መጻሕፍት አጠቃላይ ምክር ተቦጭቀው በወጡ ክርስቲያናዊ የራስ ግንዛቤ ብዙ አገዛዛዊ በደሎች መድረሳቸውን ልንረሳ አይገባም። የሂትለር መንግሥት (ምንም እንኳን የክርስትና ዋና ጠላት የነበረ ቢሆንም) አይሁድን ለማጥፋትና ዓለምን በኅይል ለመግዛት ሮሜ 13፥1 እና ቲቶ 3፥1 መጠቀሙን ታሪክ ይዘግባል – ቢያንስ ኖርዌይን በወረር ጊዜ)። ለዘረኝነት አገዛዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ያደርግ የነበረው የደቡብ አፍሪካ አገዛዝ፣ “ክርስቲያናዊ አልባሳት” የነበራቸው የምዕራቡ ዓለም ቀኝ አገዛዞች፣ የጥቁር ሕዝቦችንና የሴቶችን መብት የረገጡ መንግሥታዊ ፖሊሲዎች የቅርብ ጊዜ ትዝታዎች ናቸው። የአማኝ ሥነ-ምግባርና ሞራል ዳኛ በቅዱስ ቃሉ ላይ የተመሠረተ ኅሊና ነው። በሰላማዊ መንገድ ዘረኝነትን፣ ግፍን፣ አድሏዊነትን፣ ሕጋዊ ውርጃን፣ ጾታዊ ቀውስን፣ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን፣ ሕጋዊ ግድያን (Euthanasia)፣ የክርስቶስን ብቸኛ አዳኝነትን መናገርን “በጥላቻ ንግግር” በመፈረጅ የሚያስቀጣ ዐዋጅን እንዲሁም ተመሳስይ ቀውሶችን የማንቀበልበት ምክንያት ይኸው የኅሊና ጉዳይ ነው (ማቴ. 14፥1-13፤ ማር. 10፥42፤ የሐዋ. 5፥29)

ከላይ የዘረዘርናቸው ነጥቦች የሚያንደረድሩን ወደሚከተሉት መሠረታውያን ጥያቄዎች ነው:- “ማንኛውም መንግሥት ሥልጣኑና ኀላፊነቱ እስከምን ድረስ ነው? ማንኛውም መንግሥት ለሰላም፣ ለፍትሕና ለእኩልነት መቆም ሲገባው በተቃራኒው ጨቋኝና ኢፍትሐዊ ከሆነ፣ የቤተ ክርስቲያን ድምፅ ምን ሊሆን ይገባዋል? በኢትዮጵያ ለተከሰተው ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቀውስ የቤተ ክርስቲያን ምላሽ ምንድን ነው? በማስታረቅ ሂደት ውስጥ፣ እውነትና ምሕረት፤ ጽድቅና ፍትሕ መገናኝት አለባቸው ስንል ምን ማለታችን ነው?” በዚህ ጽሑፍ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ አልተነሣሁም። ሆኖም ጥያቄዎቹ መነሣትና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልስ ማግኘት እንዳለባቸው አምናለሁ። በመጨረሻ አንድ መልካም ነገር ጠቅሼ ነገሬን ልቋጭ። በየአብያተ ክርስቲያናቱ ጾምና ጸሎት ታውጇል፤ መልካምና ተገቢ እርምጃ ነው። ሆኖም ጾምና ጸሎት አፈግፋጊነት (quiet withdrawal) እንዳይሆን የሚያሳስብ ጥያቄ እንዳለ ልብ ልንል ይገባል። በማስታረቅ ሥራ ውስጥ፣ የተበዳዮችን ጩኸት ያልሰማ፤ እውነትና ምሕረት፤ ጽድቅና ሰላም ያልተገናኙበት ይቅርታ፣ እርቅና ፈውስ ይቻላል? 

በዚህ በጽሑፌ ለማሳሰብ እንደሞከርሁት “አገሬ በሰማይ ነውና በዚህ ምድር የሚሆነው ድሮም ከችግር ስለማይጸዳ አይመለከተኝም” ተላላነት ይመስለኛል። ቢያንስ 20% (20 ሚሊዮን) የወንጌል አማኞች ያላት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን “ስለ መንግሥትና ፍትሐዊ አስተዳደር ምን ዐይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከት ሊኖራት ይገባል?” የሚለው ጥያቄ ብስል መልስ ማግኘት አለበት። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ምስባኮችና ማኅበራዊ መገናኛዎች ከየአቅጣጫው እንደ ርችት የሚፈነጣጠቁት እይታዎችና መፍትሔዎች (አንዳንዶቹ አመለካከቶች እርስ በእርሳቸው የሚጋጩና በፖለቲካዊ ዝመቶች የተለወሱ መሆናቸው ሳይረሳ) እንዴት መቀናጀትና መጣመር እንደሚችሉ በቅጡ ማሰብ አለብን። በሌላ አነጋገር “እነዚህ ብዙ ድምጾች እንዴት አንድ ድምፅ መሆን ይችላሉ?” በማለት ራሳችንን በትህትና ልንጠይቅ ይገባል። በዐመፅ መፍትሔ አይመጣም፤ ምክንያቱም ዐመፅ፣ ዐመፅን ይወልዳል፤ ዑደቱም ከቂም፣ ድኽነት፤ ከመከራና ሥቃይ ያላረፈ ትውልድ ማትረፍ ይሆንብናል! የሚሻለው እየጾሙና እየጸለዩ፣ ችግሩ በሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚፈታበት መንገድ በማፈላለግ ቤተ ክርስቲያን የበኩሏን የጽድቅና የማስታረቅ አስተዋጽኦ ማድረጓ ይመስለኛል። ማስታረቅና የሰላም መንገድ መሆን፣ ከቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ ዜግነት ጋር አይጋጭም። ቤተ ክርስቲያን ልክ እንደ ሙሴ “… እስራኤላውያን ሲጣሉ ደረሰ፤ ሊያስታርቃቸውም ፈልጎ፣ ‘ሰዎች፤ እናንተ እኮ ወንድማማቾች ናችሁ፤ እንዴት እርስ በርሳችሁ ትጐዳዳላችሁ?” ማለት መቻል አለባት (የሐዋ. 7፥26)—ጌታ፣ “የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” (ማቴ. 5፥9)፣ እንዳለው ማለቴ ነው። ይህ የሰላም መንገድ ምን እንደሚመስልና በጽሑፌ ውስጥ ያነሣኋቸውን ጥያቄዎች በተለይም ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት እንዲሁም ክርስቲያናዊ ዜግነትን፣ መልካም አስተዳደርንና የፍትሕ ጥያቄዎችን በተመለከተ በቅርብ ጊዜ በተከታታይ በማቀርባቸው ጽሑፎች የመነሻ ሐሳብ ለማቅረብ እሞክራለሁ። አጥብቀን እየጸለይንና አጥብቀን እየጾምን፣ አጥብቀን በነገሩ እናስብ! እንደ ሕዝበ ክርስቲያን ተስፋ የምናደርገው ፍቅሩ ልዩ የሆነውን፣ መልካሙን እረኛ፣ የፍትሕና የምሕረት አምላክ ልዑል እግዚአብሔርን ነው። በቀኑ መጨረሻና የማታ ማታ ለአገራችን እውነተኛ ሰላምና ብልጽግና የሚመጣው ከራሱ ከእግዚአብሔር ነው። ከውስጥና ከውጭ የተነሡ ተግዳሮቶችን በጽናት የተቋቋመ ታሪክ እንዳለው ሕዝብ፣ በጸሎትና በአንድነት እንቁም። ከራሳችን ይልቅ፣ ለመጪው ትውልድ የተሻለች አገር እናስረክብ።
በእርግጥም ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ፣ ወደ አንተ መልሰን፤ እኛም እንመለሳለን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤ ይጠብቅም!

መጋቢ ግርማ በቀለ (/)


ይቀጥላል

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.