ስንት ዓመት፣ ስንት ምዕት ዓመት፣ ስንት “ሚሊኒየም” ኋላ እንቅር? – ጳውሎስ ፈቃዱ

ለመላው ሕይወቴ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ አነብባለሁ፡፡ ሕይወቴም መንፈሳዊ እና ሥጋዊ ተብሎ ተከፋፍሎ የተቀመጠ አይደለም፤ አንድ ሕይወት ነው ያለኝ፡፡

የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሳነብ ከምማራቸው ነገሮች አንዱ ሮማውያን ለዜጎቻቸው ይሰጡ የነበረውን የዜግነት መብትም ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ፡- የትኛውም ሮማዊ ድብደባን፣ ግርፋትን እና ስቅላትን ጨምሮ ምንም ዐይነት ሰብእናን የሚያዋርድ ቅጣት እንዳይደርስበት በሕጋቸው ተደንግጓል፡፡ ዜጎች ያለ ፍርድ ቅጣት አይደርስባቸውም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የቅዱስ ጳውሎስን ታሪክ ሲያቀርብልን በእግረ መንገዱ ይህንን ጉዳይ ጠቆም አድርጎን አልፏል፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ ያለ ፍርድ ሊገረፍ ሲል፣ ሮማዊነቱን አሳውቆ ያለ መገረፍ መብቱን አስከብሯል (የሐዋ. 22፥23-29)፡፡ በሌላ ጊዜም የጳውሎስን ሮማዊነት ያላወቁ ባለሥልጣናት በአመለካከቱ (በእምነቱ) ምክንያት አስረው ካሳደሩት በኋላ፣ በማግስቱ እንዲለቀቅ መልእክት ሲልኩለት፣ “ሮማዊ ሆኜ ያለ ፍርድ በአደባባይ ካዋረዱን በኋላ፣ በስውር ሊለቅቁኝ አይገባም፡፡ ራሳቸው መጥተው ይፍቱኝ” በማለቱ ባለሥልጣናቱ መጥተው ዜጋቸውን ይቅርታ ጠይቀው ለቅቀውታል (የሐዋ. 16፥35-39)፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን፣ በሮማ ባለሥልጣናት ዘንድ ጳውሎስ መንግሥት በማይወደው መንገድ የተሠማራ ተራ ዜጋ ነበር፡፡

ይህ ከሆነ ሁለት ሺህ ዓመት ሆኗል፡፡ ሁለት ሺ ዓመት ብዙ ነው፤ ሃያ ምዕት ዓመት ወይም ሁለት “ሚላንየም” ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ሁሉ በኋላም በአገራችን ፍትሕም ሆነ ፍርድ መጫወቻ ነው፡፡ ዜጎች ሰብእናቸውን የሚያዋርድ ግፍ በየስፍራው ይፈጸምባቸዋል፡፡ በአመለካከታቸው ምክንያት ይታሰራሉ፤ ፍርድም አያገኙም፡፡ በሕግ ቁጥጥር ሥር የዋሉ የፖለቲካ እስረኞች በምርመራ ስም ሰብእናቸውን መሬት የሚደፈጥጥ ግፍና በደል ይደርስባቸዋል፡፡ መንግሥት እንደ ወደደ ያሥራል፤ አላግባብ ያሰራቸውን ዜጎችም ራሱ ይቅርታቸውን በመለመን ፋንታ ይቅርታ እንዲጠይቁ አድርጎ ይፈታል፡፡ የጸጥታ አስከባሪዎች “ቀልባችን ያልወደደውን ዜማ አስደምጠዋል” በሚል፣ በሃይማኖታዊ በዓል ላይ የተገኙ ሕፃናትን ልሳን በጥይት ይደፍናሉ፡፡ ምን ዐይነት አራዊት ናቸው እነዚህ?

ዓለም የዜጎቹን መብት ሲያከብር ሁለት ሺህ ዓመት ዐልፎታል፤ ቢያንስ የጳውሎስ ዘመኗ ሮም ይህንን ስታደርግ ሁለት ሺህ ዓመት ሆኗታል፡፡ ለመሆኑ ከዓለም ምን ያህል ነው ወደ ኋላ የምንቀረው? ያኔ እነርሱ የነበሩበት ለመድረስ ምን ያህል ነው የሚቀረን?

“ዛሬም እዚያው ነሽ ወይ፤ ዛሬም እዚያው ነሽ ወይ?

አስሮ የሚቀጣ ዘመድ የለሽም ወይ!”

አለ የአገሬ ሰው፡፡

ሁለት ሺ ዓመት እጅግ በጣም ብዙ ነው!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.