ይድረስ ለኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ ከያሬድ ጥላሁን (የወንጌል አገልጋይ)

ቀጥታ እኔ ላይ የደረሰ ግፍና በደል ባይኖርም በሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ የሚፈጸም ግፍና በደል ያመኛል።

ስለዚህ ይህን መልዕክት የምጽፈው ከወንጌል አገልጋይነቴና ከኢትዮጵያዊነቴ የተነሳ እንጂ የማንንም ቡድን በመወገን ወይም ለየትኛውም ወገን በማድላት አይደለም። እውነትን መናገር ዋጋ እንደሚያስከፍል ባውቅም፣ እውነትን ዋጋ ከፍዬ መግዛት እንጂ አትርፌ መሸጥ አልፈልግም። ዛሬ ከሚገጥመኝ የግለሰቦችና የቡድኖች ቁጣ ይልቅ በዘመን መጨረሻ በፊቱ የምቆመው የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ያስፈራኛል። አገሬ በሰማይ እንደ ሆነ ባውቅም፣ ያየኋትን ምድራዊ አገሬን ሳልወድ ያላየኋትን ሰማያዊ አገር እወዳለሁ ብል ቃሉ ውሸታም ይለኛል። ስለ አገሬ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ ነገር ግን ለሰውም እናገራለሁ። እንደ ካህን ስለ ሰው ለእግዚአብሔር መናገር (መማለድ)፣ እንደ ነቢይ ስለ እግዚአብሔር ለሰው መናገር (ማስተማር፣ መምከር፣ መገሠጽ) ተገቢ ይመስለኛል። ልማት መልካም እንደ ሆነ እረዳለሁ ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተው ለሰው ልጅ እንጂ ለልማት እንዳልሆነ አውቃለሁ። የእግዚአብሔር ቅዱስ ማደሪያ በመልኩና በምሳሌው የፈጠረው ሰው እንጂ ሕንጻ አይደለም። የማምነውና የማስተምረው መጽሐፍ ቅዱስ ሕዝብ ለመንግስት እንዲገዛ ያዛል። ሆኖም ይኸው መጽሐፍ ቅዱስ የመንግስት ባለሥልጣናት በተንኮል ሳይሆን በጥበብ፣ በጥመት ሳይሆን በቅንነት፣ በአድሎዎ ሳይሆን በእኩልነት፣ በዝርፊያ ሳይሆን በጨዋነት፣ በግፍ ሳይሆን በፍትሕ ሕዝብን እንዲያስተዳድሩ ያዛል። መንግሥት፣ መንግሥት መሆን ሲሳነው፣ ሕዝብም ሕዝብ መሆን ይሳነዋልና። መንግሥት ለሕዝብ እንጂ ሕዝብ ለመንግሥት አይኖርምና። ይልቅ መልካም የሚያደርጉትን እያመሰገነ፣ ክፉ የሚያደርጉትን እየቀጣ፣ የሥነ-ምግባር አርአያ ሆኖ በሎሌነት መንፈስ ሕዝቡን ሲያስተዳድር ለሕግ የሚገዛ፣ አገሩን የሚወድ መልካም ሕዝብ ያፈራል።

ይህን መሠረት በማድረግ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተደጋጋሚ ሲሰነዝሩት የቆዩት ብሔራዊ ዕርቅ ለአገር ደህንነት ካለው ከፍተኛ ጠቀሚታ አንጻር በፍጥነት እንዲከናወን እማጸናለሁ። ሰላምን በማስፈን ስም በመከላከያ ሠራዊት በተለያዩ ሥፍራዎች እየተፈጸመ ያለውን ያልተመጣጠነና ኢፍትሐዊ የሆነ የኃይል እርምጃ እቃወማለሁ። አንድ ሆነው በኖሩ ሕዝቦች መሃል ልዩነት በመፍጠር አንዱን በመጋረድ፣ ሌላውን በማረድ የሚደረገው ግፍና ግድያ እንዲቆም እጠይቃለሁ። ሕዝብ ያለ አንዳች የጥፋት እርምጃ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብሶቱን በአደባባይ የመግለጽ ሕገ-መንግሥታዊ መብቱ እንዲከበር እጠይቃለሁ። መንግሥት ስህተቶቹን ማመኑ መልካም ሆኖ ሳለ ስህተቶቹን ለማረምና አገሪቱን ወደ ተሻለ አቅጣጫ ለመምራት ፍጹም የልብ ቁርጠኝነት እንዲያሳይ በእግዚአብሔር ስም እማጸናለሁ።

ያሬድ ጥላሁን (የወንጌል አገልጋይ)

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.