የአንድነቱ ፊታውራሪ – ክፍል አንድ

ባህር ዳር፡የካቲት 19/2010 ዓ/ም (አብመድ)

የሀገራችን የኢትዮጵያ አንድነት ሲነሳ ሁሌም የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ስማቸው ጎልቶ ይነሳል:: የአፄ ምኒልክ ስም ሲነሳ ደግሞ ለኢትዮጵያ አንድነት እና ነፃነት ከሀገር ውስጥ ተቀናቃኞችም ይሁን ከውጭ ወራሪ ሀይሎች ጋር ያደረጓቸው የዲፕሎማሲያዊ (ሰላማዊ) ግንኙነቶች እና ጦርነቶች ይነሳሉ::

ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ካደረጓቸው መካከል የልቼ ስምምነት፣ የደቡብ እና ምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች በሁለት ዓይነት መንገድ ለማዕከላዊ መንግሥት እንዲገብሩ ማድረግ የሚጠቀሱ ናቸው:: ከውጭ ወራሪዎች አንፃር ሲታይ ጐልተው የሚወጡት ደግሞ የውጫሌ ውል እና የዛሬ 122 ዓመት ወራሪውን የጣሊያን ጦር ድባቅ በመምታት የተገኘው የአድዋ ድል ናቸው::

ታዲያ የዛሬው ፅሁፋችን አፄ ምኒልክ ለኢትዮጵያ አንድነት ባደረጉት አስተዋጽኦ እና በተከተሉት መንገድ ላይ ትኩረት ያደርጋል። ይህንን በተመለከተ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ለ11 ዓመታት በአስተማሪነት ለሶስት ዓመታት በተማሪነት ቆይታ ከነበራቸው እና ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በአለ ፈለገሰላም የኪነ ጥበብ ትምህርት ቤት ውስጥ በኢትዮጵያ ታሪክ እና በኢትዮጵያ የሥነ-ጥበባት ታሪክ ዙሪያ እያስተማሩ ከሚገኙት የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ጋር ያደረግሁት ቆይታ ዋና የፅሁፌ መሠረት ነው። ከታሪክ ተመራማሪው ያገኘሁትን መረጃ ከማጣቀሻ መፅሀፍት ጋር እያጣመርሁ እንደሚከተለው አቅርበናል::

ተበታትና የኖረችውን ሀገር አንድ ለማድረግ አፄ ቴዎድሮሥ ፈር ቀዳጅ ይሁኑ እንጅ በኋላ ላይ አፄ ዮሐንስም ለፍተውበታል:: አፄ ምኒልክ ደግሞ አንድነቷን እውን በማድረግ ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ቁልጭ ብላ አንድትወጣ አድርገዋል::

ሆኖም ይህ ሀገርን አንድ የማድረግ ሀሣብን እውን ለማድረግ በሚደረገው ሩጫ ከፍተኛ ፈተናዎች ነበሩት:: አንደኛው በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የየአካባቢው ገዥዎች እና ባለአባቶች ጋር የሚደረግ መቆራቆሥ ነበር። ሌላው ደግሞ በአፄ ምኒልክ ጊዜ በተለያዩ አቅጣጫዎች ከፍተኛ የወራሪ ሀይል ወደ ሀገራችን እየመጡ የነበሩበት በመሆኑ ከነዚህም ጋር የሀገርን ሉዓላዊነት እና ነፃነት ለማሥከበር ከፍተኛ ትግል ማሥፈለጉ ነበር::

በመሆኑም አፄ ምኒልክ ሁል ጊዜም ለኢትዮጵያ አንድነት መረጋገጥ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው:: ይህ ሲነሳም ወራሪን ድል መምታት ማለት ነው:: ለዚህ ደግሞ ግንባር ቀደሙ አድዋ ነው:: አድዋን ከሌሎች ለየት የሚያደርገው ደግሞ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ፣ በዘመናዊ መሣሪያ እና አደረጃጀት ላይ የሚገኘውን እና ማንም ፈፅሞ ይሸንፋል ብሎ ያልገመተውን የጣሊያን ወራሪ ጦር ድል ያደረጉበት መሆኑ ነው:: በዚህም ምክንያት የሀገሪቱ ነፃነት በማያወላዳ መልኩ የተከበረበት መሆኑ ነው::

አፄ ምኒልክ ከመጀመሪያም ለሸዋ ከፍተኛ የባላባት ሥረ መሰረት ያላቸው ሰው ናቸው:: የሸዋ መሣፍንት የድሮዎቹን የአፄዎቹን ትተን ከነጋሲ ክርስቶስ ጀምሮ ያለውን ስንመለከት በማያቋርጥ መልኩ መሀል ሸዋ ላይ ግዛትን የመመሥረት ትግል ያድርጉ ነበር::
ከነጋሲ ክርስቶስ በኋላም ስብስቲያኖስ፣ አማሀ እየሱስ፣ አስፋው ወሰን፣ ሳህለ ሥላሴ፣ ሀይለ መለኮት ሁሉ በመካከለኛው ዘመን ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ባይሄዱም በፊትም አንድ ሆኖ ይኖር የነበረውን የኢትዮጵያ ህዝብ መልሰው አንድ ለማድረግ ግዛታቸውን ያሥፋፉ ነበር::

ህዝቡንም በአንድ መንግሥት ሥር እንዲጠናከር ያደርጉ ነበር:: ምኒልክም የዚህ ሥር መሰረት ያላቸው የሀይለ መለኮት ልጅ መሆናቸውን መገንዘብ ጥሩ ነው::
በዚህ መካከል ኢትዮጵያን አንድ የማድረጉን ተግባር በአፄ ቴዎድሮሥ ዘመን ሀይለመለኮት ሸዋን በሚገዙበት ወቅት ተጀመረ:: 1949 ዓ.ም አፄ ቴዎድሮሥ ወደ ሸዋ ዘምተው ሀይለ መለኮት ሞቱ:: በዚህም የሸዋ መሥፋፋት ቀረ እና የትልቋ ኢትዮጵያ አካል ሆኑ:: በእርግጥም በመካከለኛው ክፍለ ዘመን የሸዋ መሣፍንት መቀመጫ ደቡብ ወሎ ወረይሉ፣ ሳይንት እና ሰሜን ሸዋ አካባቢ ነበር::
አፄ ቴዎድሮስ ይህን የሸዋን ነገር አንድ ካደረጉ እና ግብር እንዲገብሩ ካስማሙ በኋላ አባታቸውን በሞት ያጡት አፄ ምኒልክ በምርኮ ተይዘው ወደ ጐንደር ተወሰዱ:: ታዲያ በወቅቱ አፄ ቴዎድሮስ አፄ ምኒልክን ገና በታዳጊነታቸው ወስደው ቢያስሯቸውም እንዲያው ዝም ብሎ እንደ እሥረኛ እና ተቀናቃኝ ተደርገው ሳይሆን ክብር እየተሰጣቸው ነበር ያደጉት::

ጳውሎስ ኞኞም አጤ ምኒልክ በሚለው መፅሀፋቸው አፄ ምኒልክ በአፄ ቴዎድሮሥ ትልቅ እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንዳደጉ አብራርተዋል:: “ምኒልክ በአጤ ቴዎድሮሥ ተማርከው ከተወሰዱ በኋላ እንደ እስረኛ ሳይሆን አንደ ልጃቸው ተንከባክበው ያዟቸው:: የደጃዝማችነትም ማዕረግ ሾሟቸው:: ጥቂት ቆይተው በ1856 ዓ.ም ልጃቸውን አልጣሽን በሚስትነት ዳሩላቸው” ሲሉ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ፅፈዋል::

ጳውሎሥ ኞኞ አክለውም፣ “አጤ ቴዎድሮሥ ምኒልክ እንዴት ተንከባከበው ይዘዋቸው እንደነበር በማሳያነት ከታሪክ ፀሐፊው ጉሌልም ብንወስድ ‘… ምኒልክ ከአጤ ቴዎድሮሥ ልጅ ከመሸሻ ጋር አደግኩ:: ቴዎድሮስ እንደ ልጃቸው ያዩኝ ነበር:: አባቴ ከሞቱ በኋላ ወደ ቤተ መንግሥታቸው ወሰዱኝ:: ልክ እንደልጃቸው አድርገው ይወዱኝ ነበር:: በታላቅ ጥንቃቄም አስተምረውናል::’ ብለውኛል” ሲሉም ፅፈዋል::

በዚህ ወቅት ምኒልክ እና አብረዋቸው ታሥረው የነበሩት እነ ራስ ዳርጌ ለሀገር መሞገትን፣ ሀገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ እናም ደግሞ ትልቅ ኢትዮጵያ እንዳለች ይህም ሲባል ኢትዮጵያ ይህች መሀል ሸዋ ላይ ያለችው የሸዋ መሳፍንት ይገዟት የነበረችው ሳትሆን ድንበሯ እስከባህር ድረሥ የሚሄድ መሆኑን የተረዱበት ነው::

እነዚህ የሸዋ መሳፍንት ምኒልክን ጨምሮ አፄ ቴዎድሮስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከውድቀታቸውም ከሥኬታቸውም ትልቅ ነገሮችን ተምረውበታል:: እነዚህን ነገሮች ቀሥመው ከመቅደላ እሥር ቤት ካመለጡበት ጊዜ ጀምሮ በተለይ አፄ ምኒልክ ረጅም ራዕይ ይዘው ነበር::

ያ ረጅም ራዕይ ምንድን ነው ቢባል በመጀመሪያ በሸዋ ላይ ራሥን አጠናክሮ መገኘት ነው:: ምክንያቱም አፄ ምኒልክ ወደ ሸዋ በተመለሱ ጊዜ በርካታ ተቀናቃኞች ነበሩባቸው:: አብዛኞቹ ደግሞ የእርሳቸው ዘመዶች ነበሩ:: በዚህ ሂደት ማለትም ተቀናቃኞቻቸው አሸንፈው ሸዋን በእርሳቸው አገዛዝ ሥር ካሥገቡ በኋላ የትልቋ ኢትዮጵያ አካል አድርገው በመቁጠር የሚመጣውን መመልከት አስፈላጊ መሆኑንም አፄ ምኒልክ ተረድተዋል::

ለዚህ ደግሞ ከመቅደላ እሥር ቤት የተፈቱት እነ ራስ ዳርጌም ትልቅ ድጋፍ ሆነዋቸዋል::

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.