በተጨማሪም የኒውክሌር ቴክኖሎጅ ማዕከል ግንባታ፣ ትምህርት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጅን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች በጋራ መስራት በሚቻልበት አግባብ ላይ መምከራቸውንም ታውቋል።

ሩሲያ ለኢትዮጵያ የ162 ሚሊየን ዶላር የእዳ ስረዛ ማድረጓን አስታወቀች። የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ዛሬ በተወያዩበት ወቅት ሩሲያ የዕዳ ስረዛውን ማድረጓን አስታውቃለች፡፡

ሚኒስትሮች በውይይታቸው ወቅት በሁለትዮሽ፣ አህጉራዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡ 120 አመታት ያስቆጠረው የኢትዮ- ሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አሁን ላይ እየተጠናከረ መሆኑን ዶክተር ወርቅነህ ተናግረዋል፡፡

በውይይታቸው ወቅትም ሁለቱ ሃገራት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን በማሳደግ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የኒውክሌር ቴክኖሎጅ ማዕከል ግንባታ፣ ትምህርት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጅን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች በጋራ መስራት በሚቻልበት አግባብ ላይ መምከራቸውንም ታውቋል።

ሃገራቱ በትምህርት ዘርፍ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ያነሱት ሚኒስትሩ፥ በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረትና ሩሲያ 13 ሺህ ኢትዮጵያውያን መማራቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው፥ ሁለቱ ሃገራት ካላቸው የቆየ ወዳጅነት አንጻር የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን ማሳደግ የጉብኝታቸው ዋነኛ ትኩረት መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በሃገራቱ መካከል የሚሰሩ በርካታ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ላቭሮቭ፥ ሃገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በኒውክሌር ቴክኖሎጅና በሃይል ማመንጫ ግንባታ በትብብር ትሰራለች ብለዋል።

ሩሲያ ለኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች የክህሎትና ወታደራዊ የቴክኒክ ድጋፍ እንደምታደርግ ጠቅሰው፥ የሃገራቱን የመንግስት ተቋማት የእርስ በርስ ግንኙነት የማሳደግ ስራም ይሰራል ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ሃገራቱ በአለም አቀፍ መድረክ ተመሳሳይ አቋም ለማሳየት እንደሚሰሩ በመጥቀስ በአህጉሪቱ በሚፈጠሩ ግጭቶችም የአፍሪካ ሃገራት ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ ሩሲያ ድጋፍ እንደምታደርግም በዚህ ገልጸዋል፡፡

ኤፍቢሲ

ፎቶ ዳኜ አበራ

Advertisements