የኢህአዴግ ችግር ምንድነው? – በአብርሃ ደስታ የተጻፈ

ትግራይ ህዝብ ታግሎ መስዋእት ከፍሎ አምባገነናዊውን የደርግ ስርዓት ከስልጣን በማባረሩ ሊመሰገን ይገባ ነበር። ግን ሲመሰገን አላየንም። ለምን? ምክንያቱም የደርግ አምባገነናዊ ስርዓት ቢባረርም በሌላ የኢህአዴግ አምባገነን ስርዓት ስለተተካ። የኢትዮጵያ ህዝብ ከደርግ ቢላቀቅም ከአምባገነን ስርዓት ግን አልተላቀቀም። ደርግ ቢሄድም ስርዓቱ ግን አሁን ድረስ አለ።

እንዲያውም አዲሱ ትውልድ የደርግን መጥፎነት አያውቅም። ማወቅም አያስፈልገውም። የኢህአዴግን መጥፎነት ማወቅ በቂው ነው፤ በዚሁ ትውልድ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ያለው የኢህአዴግ እንጂ የደርግ መጥፎነት አይደለም። የደርጉ አልፏል። ያለፈን ለመቀየር አትታገልም፤ በቃ ተቀይሯላ! የኢህአዴጉ ግን አሁንም አለ። ስለዚህ ልትቀይረው ይገባል። ለመቀየር ማወቅ አለብህ። እናም የኢህአዴግ ስርዓት ልንቀይረው የሚገባ ያሁኑ ጉዳያችን ነን። ደርግ ግን አጀንዳችን አይደለም፤ አልፈዋልና። ረስተነዋል። ምክንያቱም እጫንቃችን ላይ ሌላ ደርግን የሚያስረሳ አፋኝ ስርዓት አለብን።

የትግራይ ህዝብ ለነፃነትና እኩልነት ታገለ እንጂ አንድን አምባገነን በሌላ አምባገነን ለመተካት አልነበረም። አምባገነንነት ብሄር የለውም። የኢህአዴግ ስርዓት በትግራይ ህዝብ ደም ያገኘውን ስልጣን ለህዝቦች ነፃነትና እኩልነት ማስፈን ቢያውለው ኖሮ የትግራይ ህዝብ እንደተመሰገነ ይኖር ነበር። ምክንያቱም ከደርግ በኋላ ሌላ አምባገነን አናይም ነበር። ሁሉም ህዝቦች በነፃነት መኖር ቢችሉ ኖሮ ዓመፅ ባልኖረ፣ ሰላም ባልደፈረሰ እና ህዝብ ባልተጎዳ ነበር። ህዝብ የፈለገውን ነገር (ስልጣንን ጨምሮ) በሰላማዊ መንገድ ማግኘት የሚችል ከሆነ ዓመፅ አያስፈልገውም። መንግስት ማንኛውም የህዝብ ጥያቄ መመለስ ነበረበት፤ ካልቻለ ስልጣኑን ለህዝብ ማስረከብ።

ኢህአዴግ ያላደረገው/ያደረገው ነገር ምንድነው?

(አንደኛ) ህወሓት ገና ስልጣን እንደያዘ “አሸንፌያለሁ” በማለት የህዝቦችን ፍላጎት ሳያዳምጥ የራሱን አሻንጉሊቶች በየክልሎቹ ሾመ። ለምሳሌ ህወሓት “ኦነግ የኔ መሳርያ ሊሆን አይችልም” በማለት ኦነግን አባሮ ኦህዴድን መረጠ። ኦነግ በጠላትነት ተፈረጀ። ኦህዴድ የተመረጠው የኦሮሞን ህዝብ ለማገልገል ሳይሆን ህወሓትን ለማገልገል ነበር። የኦሮሞ ህዝብ የፈለገውን እንዲመርጥ ሊፈቀድለት ይገባ ነበር።

በሌሎች አከባቢዎችም የደርግ የምናምን ርዝራዦች እየተባሉ ብዙ ሰዎች በተሸናፊ ጠላቶች ተፈረጁ። የህወሓት የስልጣን ዘመን ገና ከጅምሩ በ”አሸናፊዎች” እና በ”ተሸናፊ ጠላቶች” ግንኙነት ላይ የተመሰረተ መሆኑ አመላከተ። ባንድ ሀገር ውስጥ አሸናፊና ተሸናፊ ካለ እኩልነት ሊኖር አይችልም፤ አሸናፊና ተሸናፊ እኩል አይደሉማ። እኩልነት ባልሰፈነበት ዴሞክራሲ አይኖርም። ዴሞክራሲ ከሌለ ዓመፅ ይኖራል፤ እያየነው ነው።

አሸናፊና ተሸናፊ አንድ ላይ ተባብረው ሀገር ሊያለሙ አይችሉም። በዚህ ላይ ህወሐት “ተሸናፊዎቹን” በጠላትነት ፈርጇቸዋል። በጠላትነት የፈረጅከው አካል እንዲተባበርህ አትጠብቅ። አንተን ለማሸነፍ አይተኛም። ጠላት መፍጠር አልነበረበትም። ሁሉም በገዛ ሀገሩ ተከብሮ እንዲኖር ሊፈቀድለት ይገባ ነበር። አሁን “ጠላቶች ስርዓታችንን ለማፍረስ እየሰሩ ነው ገለመሌ” ብትል ሰሚ የለህም። አዎ ጠላት ከሆነ ሊያፈርስህ ይጥራል። አሁንማ ህዝብ ሁሉ ጠላትህ ሆኗል።

(ሁለተኛው) ላለንበት የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት የሆነው የህወሓት ችግር – በአንድ ሰው ቁጥጥር ስር መዋሉ ነው። የህወሓት ተግባር በሙሉ በአቶ መለስ ዜናዊ ይከናወን እንደነበር የፓርቲው ሰዎች ይመሰክራሉ፤ የመከላከያ ስትራተጂ፣ የግብርና ፖሊሲ …. ሁሉም ነገር የመለስ እንደሆነ ራሳቸው ህወሓቶችም መስክረዋል። ሁሉም ነገር (የ40 ዓመት ዕቅዱን ጨምሮ) በአቶ መለስ የሚዘጋጅ ከሆነ ሌሎቹ የህወሓት አመራር አባላት ምን ይሰሩ ነበር? ዝም ብለው የሚሰጣቸውን የበላይ ትእዛዝ እየተቀበሉ የሌላ ሰው “ራእይ” ማስፈፀም!?

እንዲህ ከሆነ መለስ ዜናዊ ሁሉም ነገር dictate እያደረገ ሐሳቡን ያስፈፅም ነበር ማለት ነው። ስለዚህ መለስ dictate የሚያደርግ ከሆነ አምባገነን ነበር ማለት ነው። Dictator (አምባገነን) ማለትኮ A Leader Who Dictates ማለት ነው። መለስ ሁሉም ነገር ራሱ እየሰራ ለአፈፃፀም ግን ሌሎችን dictate ያደርግ ነበር በሚለው ከተስማማህ መለስ Dictator አልነበረም ማለት አትችልም።

የአንድን ፓርቲ መሪ አምባገነን (Dictator) ከሆነ ፓርቲው ውስጥ አንድ ቁልፍ ሰው ብቻ ነው ያለው ማለት ነው (ለዛም ነው ሁሉም ነገር አንድ ሰው የሚያዘጋጀው)። እናም ፓርቲው One-Man Party ይባላል። በፖለቲካ ሳይንስ እሳቤ አንድ ፓርቲ በአንድ አምባገነን መሪ የሚመራ ከሆነ አምባገነኑ መሪ ሲሞት ፓርቲውም አብሮ ይሞታል። ለዚህ ነው አቶ መለስ ሲሞት ህወሓትም የሞተው። ህወሓት የሞተችው በአባይ ወልዱ ድክመት አይደለም፤ በመለስ ዜናዊ አምባገነንነት ነው። አባይ ወሉ ኮ የመለስ ውጤት ነው፤ “የመለስን ራእይ” ለማሳካት ሲልኮ ነው ህወሓትን ይዞ ገደል የገባው። ለዚህም ህወሓት በመውደቋ ምክንያት የድሮ አገልጋዮቿ (ብአዴንና ኦህዴድ)ም ንቀዋት እያሳመፁባት ሁሉም ነገር ከቁጥጥር ውጭ ሆነ ስልጣኗም አደጋ ላይ ወድቆ አስቸኳይ ግዜ አውጃ ጣዕረ ሞት ላይ ምትገኘው። አምባገነኖች ሲወድቁ ደግሞ ብዙ ንብረት መውደምና የሰው ህይወት መጥፋት ይኖራል። ምክንያቱም አምባገነኖች ተሸንፈው እንጂ በገዛ ፍቃዳቸው የስልጣን የማስረከብ ባህል የላቸውም።

(ሦስተኛው) የቀውሱ ምክንያት ህወሓት ስልጣን ከያዘበት ግዜ ጀምሮ እስካሁን መንግስታዊ ስርዓት አለመገንባቱ ነው። በ27 ዓመት የስልጣን ዕድሜው የኢትዮጵያ ህዝብ እየተዳደረ (ይቅርታ እየተገዛ) ያለው በፓርቲ እንጂ በመንግስት አይደለም። ለዚህ ነው ለ20 ዓመት ያህል “የመልካም አስተዳደር እጦት አለ” የሚሉን። መንግስታዊ መዋቅር ካልተዘረጋ አገዛዝ እንጂ አስተዳደር አይኖርም። ምክንያቱም አስተዳደር የመንግስት ስራ እንጂ የፓርቲ ተግባር አይደለም። ስለዚህ አስተዳዳሪውን መንግስታዊ ተቋም ሳይኖር መልካም አስተዳደርን መጠበቅ ላም ባልዋለችበት ኩበት ለቀማ ነው ሚሆነው።

የአስተዳደር ተግባር ሚወጣውን መንግስታዊ ስርዓት እንዴት መገንባት ነበረበት? የመንግስት ተቋማት የሚባሉት እንደ ፍርድቤት፣ ፍትሕ ቢሮ፣ የፀጥታ አካላት እንደ ፖሊስ፣ መከላከያና ደህንነት እንዲሁም ምርጫ ቦርድ እና ሚድያ አጠቃላይ አገልግሎት ሰጪው ሲቪል ሰርቪስ የገዢው ፓርቲ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ሳይኖረው ነፃና ገለልተኛ በመሆን በህገ መንግስት መሰረት ህዝብንና ሀገርን ማገልገል ይኖርባቸዋል። ፓርቲ በመንግስት ተቋማት ላይ ጣልቃ የሚገባ ከሆነ ተቋማቱ የህዝብ ሳይሆን የፓርቲ አገልጋይ ይሆናሉ። ፓርቲ አገልጋይ ሳይሆን ተገልጋይ ይሆናል። ህዝብም አገልግሎት ሳያገኝ ሲቀር ገዢው ፓርቲ እንዲቀየርለት ይጠይቃል። ህወሐት ህዝብን ሳያስደስት 20 ምናምን ዓመት ገዝቶ ገና 40 ምናምን ዓመት ይቀረኛል ሲል ህዝብ ተስፋ ቆርጦ ያምፃል።

መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን መንግስትና ገዢ ፓርቲ መቀላቀል የለባቸውም። የመንግስት ሰራተኞች ለምሳሌ ዳኞች በፖለቲካ አመለካከታቸው ሳይሆን በሙያቸውና ብቃታቸው ሊሾሙና ሊገመገሙ ይገባል። ነፃም መሆን አለባቸው። ፖሊሶችና መከላከያ ሰራዊት አባላት ህዝብንና ሀገርን ነው መጠበቅ የነበረባቸው። ህዝብና ገዢ ፓርቲ ሲጣሉ ከገዢው ፓርቲ ጎን ቆመው ህዝብን የሚያጠቁ ከሆነ የመንግስት ሳይሆኑ የፓርቲ ናቸው።

መንግስትና ገዢ ፓርቲ ካልተለያዩ ህዝብ ለውጥ በሚፈልግበት ሰዓት አጠቃላይ ስርዓቱ ለማፍረስ ነው የሚንቀሳቀሰው። ምክንያቱም ሁሉም ተቋማት ነፃ ካልሆኑና የኔ ነው የሚለው ከሌለው ሁሉንም አፍርሶ እንደ አዲስ ከዜሮ መጀመር ይፈልጋል። በዚሁ ደግሞ ብዙ አላስፈላጊ ውድመት ይከተላል።

በሌላ መልኩ ገዢው ፓርቲ ሁሉንም መንግስታዊ ተቋማት ተቆጣጥሮ የራሱ (የፓርቲ) ካደረጋቸው ገዢው ፓርቲ ሲዳከም መንግስታዊ ተቋማቱም ይዳከማሉ። ምክንያቱም ተቋማቱ ከፓርቲ ተፅዕኖ ነፃ ካልሆኑ ጥንካሬ ስለማይኖራቸው ፓርቲ ሲዳከም የሚጠበቅባቸውን ተግባር ማከናወን አይችሉም። ይሄው ገዢው ፓርቲ ተዳከመና መንግስታዊ መዋቅሩም ዛለ፡ የሚጠበቅበትን ስራ መስራት ሳይችል ቀረ፤ እንደውጤቱም አስቸኳይ ግዜ ታወጀ። ህወሐት ነፃና ገለልተኛ ተቋማትን በመመስረት መንግስታዊ መዋቅር መገንባት ቢችል ኖሮ ለዚህ ሁሉ ችግር ባልተጋለጠ ነበር።

መንግስታዊ ስርዓት ከተገነባ ገዢው ፓርቲ የህዝብን ፍላጎት በማርካት የመራጩን ህዝብ ይሁንታ በማግኘት ስልጣን ላይ መቆየት ይችላል። ህዝብ ካልፈለገህ ደግሞ ስልጣን በመልቀቅ መንግስታዊ ስርዓቱ እንዲቀጥል ማድረግ ይቻላል። የገነባኸውን ስርዓት ዘላቂነት እንዲኖረው ማድረግ ሚትችለው የስልጣን ወንበርን የሙጥኝ በማለት ሌሎች ቡድኖች ስልጣንህን በኃይል እስኪቀሙህ ድረስ በመጠበቅ ሳይሆን የህዝብን ነፃነት በመቀበል ህዝብ የፈለገውን እንዲመርጥ በመፍቀድ ስልጣንህን በገዛ ፍቃድህ ለህዝብ በማስረከብ ነው።

ተጨማሪ ነጥብ

ጠቅላይ ሚኒስተር ማን ሊሆን ይችላል? ብላቹ ትጠይቁ ይሆናል። የፈለገ ይሁን ምንም ለውጥ አይመጣም። ሲጀመር የኢህአዴግ ችግር የመጣው ጠቅላይ ሚኒስተር ስለነበረው ወይ ስላልነበረው አይደለም። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን የለቀቀው ኢህአዴግ ሌላ ጠቅላይ ሚኒስተር እንዲመርጥ ብሎ ሳይሆን “የችግሩ የመፍትሔ አካል” ለመሆን ነበር። ችግሩ የተፈጠረው ኃይለማርያም ከመልቀቁ በፊት ነው። ችግር ፈጣሪው ደግሞ ኢህአዴግ ነው። በፓርላሜንታዊ ስርዓት ጠቅላይ ሚኒስተሩ የገዢው ፓርቲ ተወካይ ነው። ፓርቲውን ወክሎ ስልጣን ይይዛል፤ ፓርቲውን ወክሎ ይወርዳል። ስለዚህ ኃይለማርያም ፓርቲውን ወክሎ ስልጣን ከለቀቀ (በግል ጥፋት አይደለም የለቀቀው) ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስተር ከኢህአዴግ መሆን አልነበረበትም። በአውሮፓ ሕብረት ጉዳይ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስተር David Cameroon ስልጣን ሲለቅ ሌላ Theresa May መጣች እንጂ የራሱ ፓርቲ ሌላ ሰው ልምረጥ አላለም። ኢህአዴግ በስልጣን በለቀቀው ምትክ ሌላ ጠቅላይ ሚኒስተር እመርጣለሁ ካለ የኃይለማርያም መልቀቅ ምን ትርጉም አለው ታድያ?

አሁን ማንንም ይመረጥ ማንም ትርጉም የለውም። አሁን ኮ ሀገር እያስተዳደረ (እየገዛ) ያለው ሲቪል መንግስት ሳይሆን ወታደራዊው ኮማንድ ፖስት ነው።

ኢህአዴግ ሆይ ስልጣንህን በዓማፅያን በኃይል ሳትነጠቅ በገዛ ፍቃድህ ለህዝብ አስረክብ። አንድም ራስህ ያለህበት የሽግግር መንግስት ሐሳብ ተቀበል አልያም ደግሞ ፍትሓዊና እውነተኛ ምርጫ አድርግ። ዓመፅ ላንተም ለኛም አይበጅም።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.