እንደሚወራዉ ዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆነ እንዴት እንቀበለዉ የሚለውን ከአሁኑ ማሰቡ አይከፋም። እንደሚታወቀዉ ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያን አንድነትና የህዝብን መብት ለማስከበር ከህወሃት ጋር ያደረገዉ ተጋድሎ የሚደነቅና ሊመሰገንም የሚገባዉ ነዉ።

ይህንንም ብዙዎቻችን ስንገልፅ ቆይተናል። ነገር ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ትግልና የአገሪቱ ፖለቲካዊ ችግሮች ከደረሱበት ከፍተኛ ሁኔታ አንፃር የሱ መሾም የሚፈለገዉን ያህል ለዉጥ የማምጣቱ ነገር አጠራጣሪ ነዉ። የኢትዮጵያ ችግር ለመፍታት የሚያስፈልገዉ ወሳኝ ምእራፍ ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ መሰስረታዊ ሽግግር ብቻ ነዉ።

የዚህ አይነት የፖለቲካ ሽግግር በርካታ መሰረታዊ ለዉጦችን የሚጠይቅ ነዉ። ከነዚህም መካከል የፖለቲካ ሃይሎች በአገሪቱ መሰረታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ፥ ብሄራዊ እርቅ ማምጣት፥ በህዝብ ተቀባይነት ያለዉ ህገ መንግስት ማፅደቅ፥ ላልፉት 27 አመታት የተፈፀሙትን ወንጀሎች የሚያጣራ ገለልተኛ ኮሚሽን ማቋቋም፥ የምርጫ ቦርድ፥ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፥ ፍርድ ቤት፥ ፖሊስና አቃቢ ህግ የመሳሳሉትን ተቋማትን በገለልተኝነት ማዋቀር፥ የመሰብሰብን፥ የመደራጀትንና ሃሳብን በነፃነት መገለፅ የሚቻልበትን ሁኔታ መፈጠር የመሳሳሉትን እርምጃዎች የሚያካትት ነዉ። እነዚህን መሰረታዊ ጉዳዮችን መከወን ካልተቻለ አገሪቱን ከጭቆና አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ማሸጋገር አይቻልም። ይህንንም ለማድረግ ብቸኛዉ መንገድ የሽግግር መብግስት ማቋቋም ነዉ። እስካሁን እንዳየነዉ ህወሃት በሚቆጣጠረዉ መንግስት እነዚህን መሰረታዊ አላማዎች አሳካለሁ ብሎ ማሳብ ላም አለኝ በሰማይ ይሆንብናል።

የዶ/ር አብይ በጠ/ሚኒስትርነት ቢሾም እነዚህን እርምጃዎች ለመዉሰድ የሚያስችለዉ ሁኔታ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። የመጀመርያዉ እንቅፋት ህወሃት/ኢህአዴግ የሚከተለዉ ርእዮተ አለም ነዉ። አብዮታዊ ዴሞክራሲም ሆነ የልማታዊ መንግስት የሚባሉት አስተሳሰቦች ነፃ ተቋማት መኖራቸዉን የማይቀበሉና አንድ ፓርቲ ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ ሲቅይ ብቻ ነዉ አገር የምታድገዉ በሚል ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና የሲቪል ማህበራትን እንደጠላት የሚፈርጅ አስተሳሰብ ነዉ። ዶ/ር አብይ የፓርቲዉን ፖሊሲ የሚያስፈፅም ሰዉ እንደመሆኑ በእነዚህ ርእዮታለማዊ ማእቀፍ ዉስጥ የሚሰራ ሲሆን ብቻዉን ዉሳኔ እንዳይወስን በማእከላዊ ዴሞክራሲያዊነት የተተበተበ ይሆናል። ሌላዉ የመከላከያና ደህንነት ተቋማትና የኢኮኖሚ መዋቅሮች በህወሃት ቁጥጥር ስር በሆኑበት ሁኔታ ለዉጦችን ለማካሄድ እጅግ ፈታኝ ይሆንበታል ። ሌላዉ ፈተና ምንም እንኳን ዶ/ር አብይ አንዳንድ ለዉጦች እንዲኖሩ እንደሚፈልግ የታየ ቢሆንም መሰረታዊ የዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲኖር የሚፈልግና የተዘጋጀ ለመሆኑ የሚታወቅ ነገር የለም።

ስለዚህ የዶ/ር አብይን መመረጥ በራሱ እንደ ግብ ከወሰድነዉ ለሌላ ዙር ባርነት እራሳችንን ማዘጋጀት ነዉ የሚሆነዉ። የዶ/ር አብይ መመረጥን ልንቀበለዉ የምንችለዉ በአንድና አንድ መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታ ብቻ ሊሆን ይገባል። ይኸዉም ሁሉንም የፖለቲካ ሃይሎች የሚያካትት የሽግግር መንግስት ለመመስረት እንደሚፈልግ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ካሳወቀ ብቻ ነዉ። ምክንያቱን ቀደም ሲል እንደገለፅኩት አገሪቱን ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ለማሸጋገር አሁን ያለዉ ብቸኛ መንገድ ይህ ስለሆነ ነዉ። ከዚያ ዉጭ ለሚደረግ የቃላት ጅምናስቲክ ምንም አይነት ቁብ ሳንሰጥ ትግሉን አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል። አለበለዚያ ግን ከዶ/ር አብይ ጀርባ የሚያደባዉ አዉሬ ከቁስሉ አገግሞ መልሶ እንዲነክሰን ራስን አሳልፎ መስጠት ይሆናል።

Advertisements