”አማራ” የሚባል አለ ወይንስ የለም?- በኢዮብ ምህረታብ

እኮ የማይረባ ጥያቄ ነው፡፡ በታሪክ አማራ የሚባል ብሄር ነበረ አልነበረም የሚል ክርክርም ሆነ ታሪካዊ ሰነድ፣ እንዲሁ ለመደራጃ ጨረር ካልሆነ አይጠቅምም፡፡ አይጎዳምም። . . . አሁን ላይ የገበያው መጫወቻ ካርድ ምንድን ነው? ነው ዋናው ጥያቄ። አንጓው እሱ ነው።

እስኪ በደምሳሳው እንገርበው

መጀመሪያ በእነ ዋለልኝ እና መሰል ወጠጤዎችና የያ ትውልድ ደስካፒታል ትራሱ ጽንፈኛ ወፈፌዎች የብሄር ብሄረሰቦች ‘የማንነት ጥያቄ’ የተባለ ድቤ የተመታው፣ ‘የአማራው ገዢ መደብ ጨቋኝ እና ማንነት ደፍጣጭ ነው’ በሚል የተለጠጠ፣ የተጋነነ፣ ኑባሬን ያላገናዘበና ተምኔታዊ (Utopian) በነበረ የታሪክ ቅጥፈት ነው፡፡

ቀጥሎ የአማራው ገዢ መደብ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ሌሎችን ሲጨቁን፣ ሲቆርጥ፣ ሲቆራርጥ፣ ሲያርድ ፣ አርዶ ደማቸውን ሲመጥ ነበር በሚል ገዢ የመታገያና ማታገያ ጨረር ብሄረሰቦችን ከአማራው ገዢ መደብ ነጻ ለማውጣት ትግል ተጀመረ፡፡

ከድል በኋላ ሁሏም በብሄር ፌዴራሊዝም ተጠርንፋ የየራሷን ክልል መሰረተች፡፡ የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የተባለ ፓርቲ እና አማራ ክልል የተባለ የክልል መንግስት ተቋቋመ፡፡ በሂደት ድሉ ጣዕም እንዲሆነውና፣ ‘እሰይ ስለቴ ሰመረ’ የሚለው ዜማ ይደምቅ ዘንድ፣ የአማራው ገዢ መደብ የፈጸማቸውን ግፎች ቋቅቅቅቅቅቅቅ እስኪለን ድረስ፣ የሌለ አየርና ፈርቅ እየተያዘበት ተነገረን፡፡ ከዛም ብሄር ብሄረሰቦች የአማራው ገዢ መደብ ከተባለው የጠላት አገዛዝ ነጻ ከሆኑ በኋላ መብታቸው እና ማንነታቸው ተከብሮ እንዴት እንደለመለሙ፣ እንደፋፉ፣ እንደ ወፈሩ፣ እንደቀሉ ሰርክ ያስረዱን፣ ይምሉልን ጀመረ፡፡

. . . ይኸው ከሁለት አስርተ አመታት በኋላም አሁንም የቀድሞው ስርአት ስኬፕ ጎት እንደሆነ አለ።

(ጌታዬ!)

ይሄ ሁሉ የበዳይነት ዘመቻ፣የጠላት ነህ ቅጥቀጣ፣ የዘራፊ ነህ ፕሮፓጋንዳ፣ የጨፍጫፊ ነበርክ ሆረር ስቶሪ ሲሰራብህ፤ አይደለም አማራ የተባለ ብሄር፣ አማራ የተሰኘ ጾታ እና ሃይማኖት አቋቁመህ ባገኝህ አልፈርድብህም፡፡

ሰዉ ሁሉ በብሄሩ ተደራጅቶ አንተን ታሪካዊ የማርያም ጠላት አይነት ስዕል ስሎብህ፣ ብቻህን ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ኢትዮጵያዊ መንፈስ ምናምን ስትል ‘ምልኪ ነው’፣ ‘ቡዳ ነው’ ስትባል፣ እንደ ዘመኑ መጫወቻ ካርድ በብሄር ልጠርነፍና ነገር አለሙን ከአማራነት አንጻር ላወራርደው ብትል ስድና ከሃዲ አያሰኝህም፡፡

(እርግጥ ነው ያለፉት ሶስት አመታት የአማራ ብሄርተኛነት አጀማመርና ሂደት አረመኔያዊ ሸረኛነቶችና ግፎች ነበሩት፣ አሉትም)

ቤተ አምሃራ ካርታ ስሎ፣ ‘አማራ ቤኒሻንጉልን፣ አባይ ግድብንና እና አሰብን ጠቅልሎ ይገነጠላል’ የሚለው እሳቤ አስቂኝ ነው፡፡ የራሳቸውን ዘመዶች ሳይቀር በፎቶ እና በአድራሻ እየጠቆሙ በዘፈቀደ ይገደሉ የሚለው አሰቃቂ ጭካኔ ብዙ ሰው በጊዜ ከነገሩ ገለል እንዲል አድርጎታል፡፡ የተነዛው እጅግ የገነነ ጸረ ትግሬ ዘመቻ እና የአማራን በደል በሚልዮን እጥፍ ማግነንም፤ መሃል ሰፋሪ የምትለውን የዳር ላይ ተመልካች እንቅስቃሴውን እንደ Just Cause እንዳይወስደውና ሲምፓተቲክ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡

ትግሬው ከጥንት ዘመን ጀምሮ ሲኖርባቸው የነበሩ እንደ ጎንደር፣ ወልዲያና ቆቦ የመሰሉ ድብልቅ ከተሞች ላይ የነበረው ትግሬን የመግደል፣ ንብረቱን የማንደድ፣ እንዲሁም የማባረር ዘመቻም ዘመን የማይሽረው ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡:

(እርግጥ ነው፣ እርግጥ ነው)

መንግስት አማራ አለ ብሎህ ክልል ወሰንና ፓርቲ ሰጥቶህ ክደህ ኖረህ ኖረህ ትላንት አለ ብለህ እንደ አዲስ ዲስከቨሪ መጯጯህህ ያስቃል ። አማራው ተለይቶ መከነ ፤ አስር ሚልዮን አማራ ተጨፍጭፎ ቁጥሩ ቀነሰ ፤ የአማራ ሕዝብ ብዛት አርባ ሚልዮን ነው የሚሉና የመሳሰሉ የዳታ ቅሸባዎች የኮዙን አጠቃላይ ናሬሽን ጥያቄ ውስጥ ይከታሉ ። የተጋነነ ዘራፍ ዘራፍና የጄኖሳይድ አንቆለጳጳሽ መሆንም ይቀፍፋል ።

(ቢሆንም፣ ቢሆንም)

ጆከርና ቁማሩ ብሄርን ማእከል አድርጎ፣ የአማራን ገዢ መደብ ጠላትና ጨቋኝ የሚል ስዕል እስከሰጠው ድረስ፤ በታሪክ አማራ የተባለ ብሄር ኖረም አልኖረም፣ እንደ በዳይ ተደርገህ ዲፋይን በተደረክበት የብሄር ማዕቀፍ ውስጥ ሆነህ አይደለም መደራጀት፣ ቤተ ክርስቲያን ብታቋቁምም አልፈርድብህም። አይፈረድብህምም።

(ይኸው ነው)

ጌታዬ ይሄ የኔ ደምሳሳዊ እይታ ነው። ሰነድና አርካይቭ አጣቅሼ ሳይሆን ባየሁት፣ ባስታወስኩትና በታዘብኩት ላይ ተመስርቼ ነው ያወራሁት። ከላይ የተጻፈው ከደበረህ ገጽህ ላይ ዘርጥጠኝ፤ ወይንም ቦልከኝ።


በእዮብ ምህረታብ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.