ክንዱን ያፈረጠመው ስውር ሴራ በህዝቦች አንድነት ሲሸነፍ – ኢዜአ

በቡራዩ ከተማ አስተዳደር ጸጥታ መምሪያ ግቢ ተገኝቻለሁ፡፡ የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑና ተፈናቃዮችን የሚጠይቁ ሰዎች ቁጥር ብዙ ነው፡፡ በተለይ ጎረቤታሞች በፍቅር ዓይን በመተያየት፣ አብሮነትን በማንገሥ ሰውኛ ጠረን ይዘው ለዘመናት ተራርቀው እንደ ቆዩ እናት እና ልጅ እንባን ከዓይኖቻቸው ቁልቁል እያወረዱ ፍንድቅድቅ ያለ ፊት በማሳየት እርስ በእርስ ሲተቃቀፉ ላያቸው የአብሮነት ጉዳይ የቱን ያህል ጠንካራ መሆኑን ከማሳየት አልፎ ምንም እንከን መካከላቸው ባይገባ ያሰኛል፡፡

አጠገባቸው የነበሩትንና በተፈጠረው ሁከት ምክንያት ከተፈናቀሉት ወገኖች ጋር ምን ያህል ደማቸው እንደተሳሰረና ለመቼውም ቢሆን እንደማይበጠስ ረቂቅነቱን አብራርተው ለመግለጥ ቢቸገሩም የወገናቸው ፍቅር መላቅጥ እንዳሳጣቸው ከፊታቸው አልፎ መላ አካላታቸው ይናገራል፡፡ አለኝታነታቸውን መግለጽ በሚችል መልኩ ያመጡላቸውን ምግብ አብረው በመመገብ የቀደመ ኑሯቸውን መቀጠል እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡

በቡራዩ ከተማ አስተዳደር መልካ ገፈርሳ ቀበሌ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ልዩ ስሙ ፊሊ ዶሮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆነው ወጣት ወንድሙ ቶሎሳ ተከስቶ የነበረው ድርጊት ሀዘን ውስጥ ቢከትተውም፤ የአካባቢውን ማህበረሰብ የአብሮነት ገመድ እንደማይበጥስ ይናገራል፡፡

እንደ ወጣት ወንድሙ ገለጻ፤ የቄሮን ተግባር የማይወክሉ ነገር ግን በቄሮ ስም ግጭት ለመቀስቀስና አብሮ ለዘመናት የኖረውን ማኅበረሰብ ለመለያየት ሆን ብለው የተደራጁ ግለሰቦች ወደ አካባቢው መጥተው ጥፋት ማድረስ ሲጀምሩ በአካባቢው የነበሩ የኦሮሞ ተወላጆች ወገኖቻቸውን ከጉዳት ለመከላከል በቤታቸው አስጠልለዋል፡፡ እንደሌሎች ጉዳት ይደርስብናል ብለው የሰጉትንም ማንም አይለያየንም በሚል ጽኑ እምነት ወደየትም እንዳይሄዱና እትብታቸው በተቀበረበት ሰፈር ውስጥ ከትመው እንዲቆዩ ተረባርበዋል፡፡ የተደራጀው ቄሮ፣ የአካባቢው ሽማግሌዎች እንዲሁም የሃይማት አባቶች አጠቃላይ ማህበረሰቡ የተጎዱትን በማብላትና በማጠጣት ተጠምዷል፡፡ የተዘረፈውንም ንብረት ለማስመለስ፣ ቤት የተቃጠለባቸውንና የፈረሰባቸውን ነዋሪዎች ቤታቸውን በመስራት አብሮነትን የሚያስቀጥል ተግባር በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ አጥፊዎችን በማሳደድና ለጸጥታ አካል በመጠቆም በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ሌት ተቀን እየሠራ ይገኛል፡፡ ቄሮ በአገሪቱ የፌዴራሊዝም ስርዓት ስለሚያምን ከሁሉም የአገሪቱ ዜጎች ጋር አብሮ በሰላም ይኖራል፡፡

ወጣት ወንድሙ የአካባቢው ነዋሪ የተፈናቀሉትን በማያቋርጥ እርዳታ አቅፎ ወደ ቤታቸው እንደሚመልስ ይናገራል፡፡ በዚህም ህብረተሰቡ በየአካባቢው በሚያደርጋቸው ውይይቶች ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡ የተፈናቀሉት ወደ አካባቢያቸው በመመለስ የተለመደውን ማኅበራዊ ህይወታቸውን መምራት እንዳለባቸው፤ የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ፤ በንፁሐን መካከል እየገቡ ለማበጣበጥ የሚሰሩ አካላትን በጋራ ለመታገል እንደሚቆሙም ይናገራል፡፡

ቶሌራ ዲሪባ ነዋሪነቱ በቡራዩ ከተማ መልካ ገፈርሳ ወይ ብላ ጎጥ አካባቢ ነው፡፡ ሰዎች ሲጋጩ በራሱ ተነሳሽነት የማስታረቅ ልምድን አካብቷል፡፡ ‹‹በእድሜ ትንሹ አባገዳ›› የሚል ቅጽል ስም ከአካባቢው ማህበረሰብ እንደተሰጠው ይናገራል፡፡ የአካባቢው ማህበረሰብ የአብሮነት ቆይታውን ማዝለቅ እንደሚኖርበት ውስጣዊ ፍቅሩን ለመግለጽ ተዘጋጅቷል፡፡ ይህንን ናፍቆቱንና ፍቅሩን ለማወራረድ አጋጣሚውን ያገኘው ደግሞ የአካባቢው ሽማግሌዎች አባ ገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች ተሰብስበው ሰሞኑን በቡራዩና አካባቢዋ እንዲሁም አሸዋ ሜዳ በደረሰው ግጭት ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እየመከሩ ባሉበት መድረክ ላይ ነው፡፡ አሁን ለእርሱ ገነት የመግባት ያህል ደስታን የሚሰጠው አብሮ አደጎቹንና ጥብቅ ትስስር ያላቸው ጎረቤቶቹን ለማረጋጋትና ወደ ቀደመው ኑሯቸው እንዲመለሱ ከጎናቸው እንደሚቆም አለኝታነቱን መግለጹ ነው፡፡

በሰው ውርደትና ስቃይ ሰይጣናዊ እርካታ ለማግኘት ሲባል ፍጡሩን የሰው ልጅ አሽቀንጥሮ ቁልቁል መጣል ፍጹም ከሰብዓዊነት እና ከወንድማዊነት የራቀ መሆኑን የኦሮሞ ቄሮዎች እምነት መሆኑን በመግለጽ፤ በአብሮነት ላይ የተሰበቀው እኩይ አፍራሽ ትዕይንት መቅረት እንዳለበትና ከሁሉ በላይ ሊያቃቅሩ የተነሱት ከንቱ እሳቤዎች ቀብራቸው መከናወን እንዳለበት እልህ በተሞላበት አንደበቱ ይናገራል፡፡

ትንሹ አባገዳ ቴሌራ፤ ወንድሙና ጎረቤቱ የሆነውን የአካባቢው ሰው ራሱን እንደ ሰጐን አሸዋ ውስጥ ሳይቀብር እውነታውን እያየ እንዳላየ ሳይሆን የተጎዳ ወገኑ ላይ ያረፈው ቁስል የእርሱም ቁስል መሆኑን በመቀበል ወገቡን ታጥቆ መነሳቱን አብራርቷል፡፡ የቶሌራ የፍቅር ንግግር የኦሮሞንና የሌሎች ዜጎች የአብሮነታቸውን ገመድ ለመበጣጠስ የሚታትሩ የክፉዎችን ሴራ ለመበታተንና እንቅስቃሴያቸውን ለማዳከም አይነተኛ መሳሪያ ነው፡፡

በአካባቢው ምንም እንኳ በዜጎች መካከል ጸብ ባይፈጠርም ጸብ ለማስመሰል የጣሩ ግለሰቦች በፈጠሩት ግርግር ስጋት ቢፈጠርም የአካባቢው ማኅበረሰብ አንድነቱን ይበልጥ ለማጠናከርና ቅሬታዎች እንዳይኖሩ በሀገር ሽማግሌዎች ፊት እርቀ ሰላም እንዲወርድ አድርገዋል፡፡

የጋሞ ብሄረሰብ ተወላጅ የሆኑት ወይዘሮ አለንጌ መንግስቱ ሲቃ በተሞላበት የእናትነት አንደበታቸው ሰላም እንዲፈጠር ያወያዩትን አካላት በመመረቅ ንግራቸውን ሲቀጥሉ፡- ‹‹የጋሞና የኦሮሞ ህዝብ እናትና ልጅ ነን፡፡ በጋብቻ የተሳሰርን፣ በአንድ እድር የምንገለገል፤ ተዋድደንና ተከባብረን ለብዙ ዓመታት አብረን የኖርን ነን፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ከራሱ ልጅ አልፎ ጉዲፈቻ ያሳድጋል፤ ያለብሳል፤ ያስተምራል፤ ቤት ንብረት ይሰጣል እንጂ አያፈናቅልም፡፡ ሁከቱን የሚፈጥሩ አካላት ሆን ብለው ለመለያየት በማሰባቸው ነው፡፡ ለዚህ መጥፎ ተግባራቸው መቼም ቢሆን በር አንከፍትላቸውም›› በማለት በአካባቢው የነበሩትን ሀዘን ያጠላባቸው ፊቶች የተስፋ ብርሃን እንዲፈነጥቅባቸው ያደረጉት፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር ዳግም እንዳይከሰት ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበትም አክለዋል፡፡

አለማየሁ አዶሌ በመልካ ገፈርሳ ወይብላ ጎጥ ነዋሪ ነው፡፡ ተወልዶ ያደገው አርባ ምንጭ ቢሆንም፤ በዚህ ስፍራ ከ26 ዓመታት በላይ ኖሯል፡፡ የሰሞኑ ግጭት ተከሰተ በተባለበት አካባቢ የነበረ ሲሆን፤ ችግሩ የደረሰው በኦሮሞ ተወላጆች ላይም ጭምር እንደሆነ በመግለጽ፤ ከቁጥጥር ውጪ ካልሆነ በስተቀር የኦሮሞ ተወላጆች ሌሎችን ዜጎች ለማዳን ከፍተኛ ርብርብ ሲያደርጉ እንደነበር ይናገራል፡፡ በዚህም ጉዳት ሳይደርስባቸው በአካባቢው ማህበረሰብ ቤት ተጠልለው የሚገኙ ሰዎች መኖራቸውን ተናግሯል፡፡ ‹‹ተሰደን ከመጣንበት አካባቢ በኦሮሚያ ቤት ሰርተን የኦሮሞን ህዝብ ወተት ጠጥተን ጋብቻ መስርተን እየኖርን ነው፡፡ አንድነታችን የሚያማቸው ሰዎች ሊበታትኑን ያደረጉት እንጂ የኦሮሞን ቄሮ የማይወክል የሰርጎ ገብ ድርጊት ስለሆነ ቦታ አንሰጠውም ሲል ክንዱን ያፈረጠመውን ስውር ሴራ መርታት እንደሚቻል አሳይቷል፡፡ አዎ በቡራዩ ይህ በመከሰቱ የኦሮሞና የጋሞ ብሄረሰብ መካከል ምንም ችግር ያለመኖሩን በአንደበታቸው መስክረው አረጋገጡ፡፡ የዚህ መልካም ተግባር ምሳሌነትም በአርባ ምንጭ ሰሞኑን በተግባር ታይቷል፡፡ በስሜት የተገፋፉ የአርባ ምንጭ አንዳንድ ወጣቶች ጥቃት ሊሰነዝሩ ሲሉ የመልካም አስተሳሰብ ባለቤት የሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች አብሮ በኖረ ሕዝብ ላይ ጉዳት ማድረስ ባህላችን አይፈቅድም በሚል ቄጤማ ነጭተው ተንበርክከው በአገሩ ባሕል መሰረት በመማፀናቸው ሊደርስ የነበረውን ጥቃት አስቀርተዋል፡፡ ይህ በጎ ባህላዊ ልማዳችን ክፉ ለሚያስቡ አርአያ ሊሆን ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ጋዜጣ መስከረም 11 ቀን 2011 ዓ.ም

በአዲሱ ገረመው

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.