በተለወጠች ኢትዮጵያ ስለምናምን እንጂ 97 ላይ በመንግስት ወታደር ሲተኮስብን እርስዎ ኢህአዴግ እንደነበሩ እረስተን አይደለም

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የአዲስ አበባ ወጣት ስራ አጥ የተደረገው፤ በሱስ እና ተስፋ መቁረጥ እንዲገፋ የተደረገው፤ በብሔር አልቧደንም ስላለ በየግዜው በአፈሳ የሚሰቃየው በእርስዎ ድርጅት ኢህአዴግ ነው፤ እኛ እርስዎን የደገፍነው በተለወጠች ኢትዮጵያ ስለምናምን እንጂ 97 ላይ በመንግስት ወታደር ሲተኮስብን እርስዎ ኢህአዴግ እንደነበሩ እረስተን አይደለም።

ድርጅትዎ ኢህአዴግ ውሃ እና መብራት እያጠፋ ስለ ኑሮ እየተብሰለሰልን ሌላ ነገር እንዳንጠይቅ እንደሚያደርገን እናውቃለን፤ ስራ አጥ ሆነን እንድንንከራተት፤ ጫት ቤት እና መጠጥ ቤት በየ ጢሻው ከፍቶ ኑሯችንን ያጎሳቆለን፤ በልማት ሰበብ ከኖርንበት አፈናቅሎ የበተነን፤ ክልል 14 የሚለውን አጥፍቶ ኦሮሚያ ክልል የከተተን፤ ባለቤት አልባ ለማድረግ ከመኖሪያችን እያፈናቀለ የበተነን የ 97ን ምርጫ ቂም ለመወጣት እና የያዝነውን ኢትዮጵያዊነት ለመምታት ያሴረው ኢህአዴግ እና የ ኢህአዴግ የቂም በቀል ፖለቲካ ብቻ ነው።

በኢትዮጵያ መለወጥ ስለምናምን ኢትዮጵያ ብለው ሳይጨርሱ ልንደግፍዎ አደባባይ የወጣነው በሃገራችን ድርድር ስለማናውቅ፤ ዘረኛ ስላልሆንን ነው፤ አዲስ አበባ የእርስዎን ምስል ለብሶ እየሞትኩ ቢሆንም ዶክተር አብይን አደራ የሚል ወጣት ያገኙበት እንጂ፤ ሊገልዎት ቦንብ ያፈነዳ፤ ሰው ዘቅዝቆ የሰቀለ ወጣት ያዩበት ከተማ አይደለም።

ስንደግፍዎት፤ ኢህአዴግ ስላልሆኑ አይደለም፤ ስንደግፍዎት፤ኑሯችን ተስተካክሎ፤ ጥያቄያችን ተመልሶ፤ ወይም ከእኛ ብሔር ነዎት ብለን አይደለም፤ እኛ ከብሔር በፊት ሰው የምናከብር፤ ስለ ሃገራችን ደረታችንን የምንሰጥ ህዝቦች ነን፤ እንደሚሰሙት ሰፈር እንጂ ብሔር አናውቅም፤ ኢህአዴግ ሲገለን እርስዎም ኢህአዴግ ነበሩ፤ ይቅርታ ያደረግንልዎት በሃሳብዎ ተስማምተን ለውጥ ያመጡልናል ብለን አምነን ነው፤ ከእኛ ጉዳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ ስለሚበልጥብን።

የኦነግ ደጋፊዎች አደባባይ ሲቀቡ፤ ሃውልት እናፈርሳለን ሲሉ ተቃውመናል፤ ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት አፈንግጠው ሴት ሲደፍሩ፤ ሰው ሲገሉ በሰላም ወጥተን ልክ እንዳልሆነ ጮኸናል፤ መንግስት የተኮሰብን ግን እኛ ላይ ነው፤ መንግስት ጦላይ ያሰረን ግን እኛን ነው፤ ለውጥ ነው ብለን ዝም ብንል፤ መንግስትዎ ስልጣኑን ባረጋገጠ ማግስት፤ ሰላማዊ የሆንን እና ለለውጥ ቀድመን የተሰለፍን ህዝቦችን ቅስም ለመስበር፤ ዘረኞች የህግ ከለላ አግኝተው በሰላም እየኖሩ እኛ ከእባብ እና ዘንዶ ጋር ውለን ማደራችን ሳያንስ ሹመኞችዎ እየተሳለቁብን ይገኛሉ፤ እርስዎም ህገመንግስቱ ፅፎ የሰጥዎትን የዜጎችዎን በሰላም የመኖር መብት መጠበቅ ዘንግተው ስንታሰር ዝም ብለዋል፤ ያለ ህጋዊ መሰረት አስራችሁ ፈታችሁን፤ እልል አታስብሉንም፤ በእዚህ እንደማንታለል ያውቁታል ስለሆነም።

• መንግስትዎ ያለ ህግ አግባብ ያሰራቸውን የአዲስ አበባ ወጣቶች እንዲፈታ በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ

• የውሸት ሪፖርት እየፃፉ በአዲስ አበባ ተገለዋል ያሉ ሹመኞችዎ በአደባባይ እውነቱን እንዲያወጡ በአስቸኳይ እንዲጣራ

• የኦሮሞ ብሄርን የበላይነት ለማንገስ በአዲስ አበባ አስተዳደር እየተፈፀመ ያለውን የአላግባብ መታወቂያ የማደል፤ የቦታ ስጦታ ሴራ የማንቀበለው እና በራሳችን የመተዳደር ህገመንግስታዊ መብታችን እንዲከበርል

• አዲስ አበባ ተወልደን እየኖርን ባለቤት እንዳልሆንን በየዜና ማሰራጫው እየተደሰኮረ መንግስትዎ በቸልታ ማለፉ፤

እርስዎም ሆነ ሹመኞችዎ የአዲስ አበባን ህዝብ ንቃችሁ፤ ለለውጡ ያሳየውን ፍፁም ድጋፍ እና ከጎንዎ በቦንብ እየተደበደበ እንኳን ድጋፍ ያልነሳዎትን ህዝብ ውለታ ዘንግታችሁ፤ አሁንም ስቃዩ እንዳያቆም ቸልተኛ በመሆናችሁ በይፋ ይቅርታ ልትጠይቁን እና ስህተቶቹንም ልታርሙ ይገባል።

ተቀራርበን እና ተባብረን ትልቋን ኢትዮጵያ መስራት እንደምንችል እናምናለን፤ ብዙ ያልተፈቱ የሃገራችን ችግሮች እንዳሉ እናውቃለን፤ ሰው በዜግነቱ ተከብሮ ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተጠብቆ የሚኖርባትን ኢትዮጵያ እንናፍቃለን። ስህተት ስትሰሩ ግን ዝም አንልም፤ እኛ በሃሳብ የበላይነት እናምናለን፤ ኢህአዴግ ሃሳቡን ሲተቹት ፀረ ሰላም ሃይሎች ብሎ እንደለመደው፤ ዛሬም ስህተታችሁን ስንነግራችሁ ፀረ ለውጥ እንደማትሉን እምነት አለን፤ ለሃገራችን ሰላምና ብልፅግና የቆምን፤ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ችግር የሚመለከተን ህዝቦች ነን።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መንግስትዎ ይህን ችግር የማይፈታ ከሆነ ግን ለመብታችን የሚከፈለውን ዋጋ ለመክፈል፤ ለአንድነታችን መረጋገጥ ስንል ጫፍ ድረስ እንደምንደርስ ይወቁልን።

ጥቅምት 7፤ 2011ዓም

አዲስ አበባ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.