Tag: addis ababa

የኦሮሞ ህዝብ ከከተማዋ ያለው ጉዳይ ከንቲባ ከኛ ይሁን የሚል አይደለም – ጃዋር መሀመድ


የፊንፊኔ ከንቲባ ኦሮሞ መሆኑ የጦዘ ክርክር ማንሳቱ እያየን ነው። ክርክሩ የተጠበቀ ቢሆንም የመከራከሪያ ነጥቦቹ ትንሽ ገርመውኛል።

Continue reading “የኦሮሞ ህዝብ ከከተማዋ ያለው ጉዳይ ከንቲባ ከኛ ይሁን የሚል አይደለም – ጃዋር መሀመድ”

Advertisements

ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስን ለከንቲባነት ኢንጂነር ታከለ ኡማን ለማዘጋጃ ቤት ሓላፊነት – ኤርሚያስ ለገሰ


ታሪካዊ መንደርደሪያ

ወቅቱ የኢትዮጵያ የሚሌኒየም አመት (2000 ዓም) መገባደጃ አካባቢ ነበር። የአዲስ አበባ ዳግም ምርጫ ተካሂዶ የከተማው ከንቲባ፣ ካቢኔ ፣ የክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚና ካቤኔዎች በኢህአዴግ ቢሮ የምንመድብበት ነበር። ስራው በፍጥነት መሰራት ስለነበረበት አቢይ ኮሚቴ እና ንዑስ ኮሚቴ ተደራጅቶ የሚፈፀምበት ነበር።

አቢይ ኮሚቴው የሚመራው በአቶ በረከት ሲሆን ተመልማዬችን ፕሮፓዛል ይዘን የምንመጣው የኮሚቴው አባላት አቶ አርከበ እቁባይ፣ ህላዌ ዬሴፍ፣ ካሚል አህመድ፣ ፀጋዬ ኃ/ማርያም፣ ፍሬህይወት አያሌው፣ ይሳቅ አበራ(ቆሪጥ) እና እኔ ነበርን።

እናም አቢይ ኮሚቴው በበረከት ቢሮ ተቀምጠን ለመዲናይቱ ከንቲባ፣ ምክትል ከንቲባና ካቢኔ የሚሆኑትን መምረጥ ጀመርን። ለአዲስ አበባ ምክርቤት ከተወዳደሩት አባላት ውስጥ ለከንቲባነት እጩ ሆነው የቀረቡት አቶ ኩማ ደመቅሳ፣ ወይዘሮ አስቴር ማሞ እና አቶ መላኩ ፈንታ ነበሩ።

በመጀመሪያው ዙር በረከት በአቶ መላኩ ፈንታ ላይ ቅሬታ በማንሳቱና ብአዴን ባለበት እንዲቀጥል ትፈልጋለች በማለቱ መላኩ ፈንታ ውድቅ ተደረገ።በክርክሩ ወቅትም ሳይነሳ ቀረ። እናም የተቀሩት ሁለቱ ኦህዴዶች ሆኑ። ኩማ ደመቅሳና አስቴር ማሞ። አሁንም በረከት የድርጅቱ (የባለቤቱ ወይዘሮ አዜብ በተለይ) ፍላጐት ወይዘሮ አስቴር ማሞ ከንቲባ እንድትሆን ነው በማለት እንቅጩን ነገረን። ሁላችንም ተቃወምን። በተለይ አርከበ በንዴት እየተንጨረጨረ ቅሬታውን አቀረበ። ይህም ሆኖ የድርጅቱ እና የሚስታቸው ውሳኔ በመሆኑ የሚቀለበስ ነገር እንደሌለ ተነገረን። የመጨረሻ ቀጠሮ ለሚቀጥለው ሳምንት አስረን ተለያየን።

የቀጠሮው ቀን እስኪደርስ የነበሩት ቀናት የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ለነበርን ሰዎች ከፍተኛ ሴራ ከጠነሰስንበት ጊዜያቶች የላቀውን የሚይዝበት ነበር።

በአንድ በኩል በካድሬዎች አማካኝነት የአዲስ አበባ ሕዝብ በወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር የነበረው ኩማ ደመቅሳ ከንቲባ እንዲሆን መፈለጉት አሰራጨን። ከሰላሳ ሺህ በላይ መጠይቆችን በማዘጋጀትና በመሙላት 75 በመቶ ኩማን፣ 15 በመቶ መላኩ ፈንታንና 3 በመቶ ወይዘሮ አስቴርን ከንቲባ ሆነው ማየት እንደሚፈልግ አመላከትን።

በሌላ በኩል ተነባቢ ለነበሩ የግል ጋዜጦች ቀጣዩ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ እንደሚሆን የውስጥ መረጃ በመስጠት ጋዜጦቹን በኩማ ፎቶ አደመቅናቸው። አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ድርጅቱ ሃሳቡን ቀይሮ ኩማ ደመቅሳን ከንቲባ ለመመደብ ተገደደ።

ከሁሉም አስቂኙ ነገር አቶ ኩማ ከንቲባ እንደሚሆን የተነገረው ምክርቤቱ ሊጠራ በዋዜማው ስለነበር ድንግርግሩ ወጥቶ ነበር። በቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ያነበበው የአስተዳደሩ የአመቱ መሪ እቅድ የተመለከተው የእለቱ እለት ነበር። በአካልና በስም የማያውቃቸውን የካቢኔ አባላት ጽብፃብ ኮስተር ብሎ ሲያነብ ራሱ ያዘጋጃቸው ይመስል ነበር። ኩማ ደመቅሳ እንዲህ ነበር።

***

ከላይ የተጠቀሰውን ታሪክ ወደ ኃላ ሄጄ የማነሳበት የተወሰኑ ምክንያቶች አሉኝ። እስከ አሁን ድረስ የአዲስ አበባ ከንቲባነት የሚገኘው በህዝብ ምርጫ ሳይሆን በፓርቲ ምደባ እና ክፍፍል ነው። ከንቲባውም ተጠሪነቱ ለፓርቲውና ለመደበው ግለሰብ ነው። ይሄ ባልተለወጠበት ሁኔታ የፓርቲ ምደባ ላይ መሻኮትና እርስ በራስ መደባደብ የለውጥ ሂደቱን እንዳይፋጠን ከማድረግ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም። ከዚህ አንፃር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ “ በሁሉም መራጭ ህዝብ ያልተመረጠ ሰው ፕሬዝዳንት (“ከንቲባ”) ነኝ ሊል እንደምን ይቻለዋል?” በማለት የተናገሩትን ማስታወስ ይበጃል።

እናም ጠቅላይ ሚኒስትሩን መጨቅጨቅ ያለብን በቀጣዩ ምርጫ የአዲስ አበባ ከንቲባ የሚሆነው ከ1 ሚሊዬን የአዲሳባ መራጭ ውስጥ ከግማሽ ሚሊዬን በላይ የመረጠው ብቻ እንዲሆን ቻርተሩን እንዲያሻሽሉልን ነው። የአዲስ አበባ አጠቃላይ መራጭ ህዝብ ወደ አንድ ሚሊዬን ይጠጋል የሚል ታሳቢ ወስጄ ነው። እናም ይሄ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ ፍፁም ፍላጐት ከመሆኑም በላይ የመዲናይቱን የፓለቲካ ሽኩቻና የዘር መጓተት ተቋማዊ በሆነ መንገድ የሚፈታ ይሆናል። አንድ ድምፅ ለአንድ ሰው የሚል መርሆ ያለው የፕሮፌሰር መረራ ፓርቲም በውሳኔው ደስተኛ እንደሚሆን አልጠራጠርም። መቼም በዚህ የውሳኔ ሃሳብ የሚከፋ ሰው ካለ ወይ ዲሞክራሲ አልገባውም አሊያም ለአዲስ አበባ ህዝብ ክብር የለውም። አልፎ ከሄደም የአዲስ አበባን ህዝብ ይጠላል። ድፍን የአዲስ አበባ ህዝብ በግሉ የምርጫ ውሳኔ ከንቲባውን መርጦ ሲደሰት የሚከፋው ከሆነ ቦታው አማኑኤል መሆን አለበት።

ከዚህ በተጨማሪም ከግማሽ ሚሊዬን በላይ የሚሆነው የአዲስ አበባ ህዝብ የመረጠው ከንቲባም ደረቱን ነፍቶ “ ሕዝብ የመረጠኝ ነኝ!” ማለት ይችላል።ትችላለች።

***

ወይዘሮ ዳግማዊ ሞገስ የአዲስ አበባ ከንቲባ

ከላይ የተቀመጠው የቻርተር ማሻሻያ የውሳኔ ሃሳብ ወደ ተግባር እስኪለወጥ ድረስ የሚመደበው ከንቲባ በህዝብ ያልተመረጠ በመሆኑ ራሱን እንደ ሽግግር ከንቲባ መውሰድ ይኖርበ(ባ)ታል። ይሄ(ቺ) ከንቲባ ጊዜያዊ እንደመሆኑ(ኗ) መጠን በተቻለ መጠን የህዝቡን ውስን ፍላጐቶች ቢያ(ታ)ሟላ ጥሩ ይሆናል።

በመሆኑም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨዋውን ፣ ያላሳፈሮትን፣ በችግር ጊዜ ከጐኖ ቆሞ ያኮራዎትን የአዲስ አበባ ነዋሪ ፍላጐት ለማሟላት ወይዘሮ ዳግማዊ ሞገስን በከንቲባነት ፣ ኢንጂነር ታከለ ኡማንን ደግሞ በማዘጋጃ ቤት ሓላፊነት እንዲመርጡ ፍቃድሆ ይሁን። የዛሬ ውሳኔዎትን መልሰው አጢነውት ሽግሽጉን በአስቸኳይ ይፈፁሙ። አለበለዚያም ምክንያቶን ያስረዱ።

ወይዘሮ ዳግማዊ ሞገስ የአስተዳደሩ ከንቲባ እንድትሆን የማቀርባቸው ምክንያቶች ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው።

1. ዳግማዊት አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገች ናት። የኮልፌ ቀራንዬ ልጅ የሆነችው ዳግማዊት አዲስ አበባን ከግር እስከ ራሷ ታውቃታለች። የህዝቡን ማንነት እና ስነ ልቦና ጠንቅቃ ትገነዘባለች።

2. ዳግማዊት ወደ አዲስ አበባ መስተዳድር ስናመጣት የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መምህር ነበረች። በዛን ሰአት እድሜዋ ከ21 እስከ 23 አመት ውስጥ እንደነበር አስታውሳለሁ። በአሁን ሰአትም እድሜዋ ከ33 የሚበልጥ አይመስለኝም። ዳግማዊት በዩንቨርስቲው መምህር ሆና ልትቀር የቻለችው በትምህርቷ በጣም ጐበዝና የከፍተኛ ማዕረግ ምሩቅ ስለነበረች ነው። የዩንቨርስቲ መምህርነቷን ለቃ ስትመጣ በፍፁም ህዝብ የማገልገል ፍላጐት ሰንቃ የመጣች ሲሆን በዝዋይ አላጌ በነበረው የሁለት ወር ስልጠናም በቅርበት ማረጋገጥ የቻልኩት ሁለንተናዊ እይታዋን ነው።

በነገራችን ላይ በአንድ ወቅት ዩንቨርስቲውን ለቃ መምጣቷ ቅር እንደሚያሰኘኝ ሳልደብቅ ነግሬያታለሁ። ያለምንም ጥርጥር በዩንቨርስቲ ቆይታዋ ቢራዘም ኖሮ ሶስተኛ ዲግሪዋን ይዛ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የምትወዳደርበት አቅም ታዳብር ነበር።

3. ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የአዲስ አበባ ምክርቤትና የካቢኔው አባል ስለሆነች ክቡርነትዎ እሷን ጊዜያዊ ከንቲባ ለማድረግ ህገ መንግስትና ቻርተር መጣስ አይጠበቅቦትም። በአዲስ አበባ ታሪክም የሚያስቀምጡት ጥቁር ጠባሳ ሳይሆን የተስፋ ብርሃን ይሆናል። ወጣቷ ወይዘሮ ከክፍለ ከተማ ጀምሮ የመዲናይቱን ቢሮክራሲና አሰራር የተመለከቱት ስለሆነ የእሮሶ ድጋፍ ከተጨመረበት በአጭር ጊዜ የለውጥ ሃዋርያው መሪ ትሆናለች።

4. እስከማውቀው ድረስ ወይዘሮ ዳግማዊት ሌብነት እና ዝርፊያን የምትጠየፍ እንስት ናት። ሙሉ ፍላጐቷ ህዝብ የማገልገል ስለሆነ እንደዚህ አይነት ራስን ዝቅ የሚያደርግ ወራዳ ስራ ውስጥ እጇን የምትነክር አይመስለኝም። እርሶም በአሁን ሰአት የምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሰጧት ይሄን ተመልክተው ይመስለኛል።

5. ወጣት ዳግማዊት የጠንካራ ሴት ተምሳሌት ናት። ይህቺን አርአያ የምትሆን ጠንካራ ሴት እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በከንቲባነት መሾም ትልቅ ክብር ነው። የሴትየዋ ስም በታሪክ ውስጥ ሲነሳ የእርሶም ስም አብሮ ይነሳል። እስቲ ይታዮት ከእለታት አንዲቷ ቀን የማዘጋጃ ቤት የምክር ቤት አዳራሽ ገብተው የተሰቀሉትን ከመጀመሪያ እስከ ዛሬ የነበሩ ከንቲባዎች ውስጥ የአንዲት ሴት ፎቶ ብቻ ተሰቅሎ ሲመለከቱ የሚሰማዎት ስሜት? ያውም በእርሶ ዘመን። የዛኔ እኛም “ታሪክ በታሪክ ሰሪዎቹ ተሰራ!” ብለን ለመፃፍ እንታደላለን። እናም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይረፍድብዎ ታሪክ ይስሩ።

ኢንጂነር ታከለ ኡማን የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሓላፊ

ኢንጂነር ታከለ ኡማንን የማዘጋጃ ቤት ኃላፊ እንዲሆን የምፈልግበት ምክንያት በአጭሩ ልግለፅ። እንደገባኝ ከሆነ ኢንጂነር ታከለን የፈለጉበት ምክንያት በዋናነት የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጅ በመሆኑ ሳይሆን የእርሶ የለውጥ ሐዋርያ ቡድን ውስጥ የታቀፈ ሰው ስለሆነ ይመስለኛል። ባይሆን ኖሮ የድርጅቶ ፕሮግራም የተገለፀበትን ህገ መንግስት እና ቻርተር እስከ መጣስ የሚያዘልቆት አይመስለኝም። እንደዚህ ከሆነ ዘንዳ ህግ ሳይጥሱ ይሄን የእርሶ የለውጥ ሐዋርያ ቁልፍ ቦታ ላይ መመደብ የሚቻልበት እድል አለ።

በእኔ እምነት በአዲስ አበባ የስልጣን እርከን ውስጥ ሶስት ቁልፍ ቦታዎች አሉ። ከንቲባ፣ የማዘጋጃ ቤት ሐላፊ እና የፓርቲ ጽህፈት ቤት ሐላፊ። እነዚህን ሶስት ቦታዎች በእርሶ የለውጥ ሐዋርያ ቡድን መቆጣጠር ከቻሉ ሌላው እዳው ገብስ ነው። ዛሬ የማዘጋጃ ቤቱ እና የፓርቲው ጽህፈት ቤት የተያዘው የቀን ጅቦች በሆኑት የህውሓት ካድሬዎች በሆኑት ሓይሌ ፍስሃና ተወልደ ነው። እነዚህን አደገኛ ሰዎች ወደ መጡበት ማሰናበት ጊዜ የሚሰጠው አይደለም። ለበለጠ መረጃ አጠገቦት ቺፍ ኦፍ ስታፍ ያደረጉትና የቀድሞ የአዲስ አበባ ጥቃቅን ሐላፊ የነበረውን ፍፁም አረጋ መጠየቅ ይችላሉ።

ግልባጭ: ለፍፁም አረጋ (ቺፍ ኦፍ ስታፍ)

ለማ መገርሳ( ፕሬዝዳንት)

ስርዓቱ ይሆናል እንጂ አገር አትበታተንም


በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ምክንያት የብዙ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፤ ከ75 ሺህ በላይ የሚሆኑ የኦሮሚያ ተወላጆች አካባቢያቸውን ጥለው መፈናቀል እንዲሁም ለሺህዎች ንብረት መውደምም ምክንያት ሆኗል።

የክልሎቹ መንግሥታት ግን እርስ በርስ መወነጃጀልን መርጠዋል። ምንም እንኳን ይሄ እሰጥ እገባ እየቀለለ የመጣ ቢመስልም ግጭቶቹ እንዳልበረዱም፤ የሚፈናቀልም ሰው ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ በቅርቡ አሳውቀዋል።

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የድርጅቱ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ማዕከላዊው መንግሥት ችግሩ በተከሰሰበት አካባቢ በፌዴራል አካላት፣ በመከላከያና በፖሊስ ኃይል አማካኝነት ዋና ዋና መንገዶችን በመቆጣጠር ችግሩን አብርዷል። እርሳቸው ይሄንን ቢሉም በክልሎቹ መካከል እስካሁን ግጭቱ ያልተፈታ መሆኑ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ነው።

ባስ ሲል በቅርቡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ ከስልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውም ግርምት ፈጥሯል። አቶ ሽፈራው ኢህአዴግ ከያዘው የመተካካት ስርዓት ጋር የተያያዘ ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ከመንግሥት የስልጣን ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ ልልቀቅ ማለታቸው ያልተለመደ መሆኑንም አቶ ሽፈራው አልደበቁም።

ምንም እንኳን አባ ዱላ ለመልቀቅ የጠየቁበትን ምክንያት ለወደፊቱ እገልፃለሁ ቢሉም፤ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል በተነሳው ግጭትና መፈናቀል ማዕከላዊው መንግሥት የሰጠው አዝጋሚ ምላሽም ቅር እንዳሰኛቸው የቅርብ ሰዎች እየተናገሩ ነው።

በኦሮሚያ የነበረው ተቃዉሞImage copyrightGETTY IMAGES

አገራዊ ተቃውሞዎች

በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች አገሪቷን ያናወጠ ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቷል። ከዓመት በላይ የዘለቀው ይህ ተቃውሞ የተነሳው ጊንጨ አካባቢ ሲሆን፤ ይሄም የጪልሞ ጫካ ወደ ግል ይዞታ በመዛወሩ የተነሳ ነበር። ይሄም በአገሪቱ ላይ አከራካሪ የሆነውንና ለዘመናት መመለስ ያልተቻለውን ‘መሬት የማን ነው?’ የሚለውን ጥያቄ ከኋላ አንግቦ የተነሳ ነው። በርካታ ገበሬዎች በልማት መነሳት ያመጣቸውንም ቀውሶች ያጋለጠ ነበር።

የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ወረዳዎች የተቀናጀ ማስተር ፕላን ሊያመጣቸው የሚችሉ ከፍተኛ መፈናቀሎችን በመቃወምም ብዙዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

ይህ ከመሬት ጋር ተያይዞ የተነሳው ጥያቄ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ብሄርን መሰረት ያደረገው ፌደራላዊ ሥርዓት ያልመለሳቸው ጥያቄዎች ናቸው።

በተመሳሳይ በአማራ ክልልም ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ችግሩም እሳካሁን መፍትሄ አልተገኘም የሚሉ ሰዎች ጥያቄውን በማንሳት ላይ ናቸው።

ሥርዓቱ የክልል መንግሥታት ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት፣ የራሳቸውን ተወካዮች የሚመርጡበት፣ የራሳቸውን ቋንቋ የሚናገሩበትን ሥርዓት መመስረት፣ ቀድሞ የነበረውን የዜግነት እሳቤን መቀየር የሚል ቢሆንም የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞች በትክክል ተግባራዊ እንዳልተደረገ ይተቻሉ።

ታዋቂው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና ተንታኝ ጆን ማርካኪስ “ይሄ ሁሉ ግን የተደረገው ህዝቡን ፀጥ ለማስባል እንጂ ስልጣንን ለማጋራት አልነበረም፤ ፌደራሊዝሙ በኢህአዴግ የተሰላ ጥረት ነው” ይላሉ።

“ስልጣን አሁንም በማዕከላዊው መንግሥት ቁጥጥር ስር ነው፤ ፌደራል መንግሥቱ ስልጣንንም ሆነ ሀብትን በቁጥጥር ስር አድርጎ ለማከፋፈልም ሆነ በጋራ ለመጠቀም ዝግጁ አይደለም። ይኼ አካሄድ ደግሞ ለሥርዓቱ ትልቅ ጠንቅ ነው፡፡ የአንድን አገር ህልውና ለመጠበቅ ኃይል ብቻውን በቂ አይደለም፡፡” በማለት ይጨምራሉ።

ሕዝቦች ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት፤ ስልጣንና ሀብትን የሚጋሩበትን ሥርዓትን ይህ መንግሥት መፍጠር አልቻለም የሚሉት የመድረክ ምክትል ሊቀ-መንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙላቱ ገመቹ ናቸው። “ራስን በራስ የማስተዳደር መብት አልተሰጠም፤ አሁንም ለይምሰል ነው እንጂ ለሥርዓቱ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ከላይ በማስቀመጥ በተዘዋዋሪ አሃዳዊ በሆነ መልኩ በጠመንጃ የሚተዳደሩበት ሥርዓት ነው።” ይላሉ።

የዲሞክራሲ እጥረት

የተለያዩ ምሁራን እና የፖለቲካ ተንታኞች የችግሩን ምንጭም ሆነ መፍትሄውን በተለያየ መነፅር ይመለከቱታል። የቀድሞ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ጀነራል አበበ ተክለሃይማኖት (ጆቤ) “ፈተና የሌለበት ሥርዓት የለም” በማለት በአገሪቷ የተከሰተውን አመፅና ግጭት በአሉታዊነቱ ብቻ አይመለከቱትም። በአገሪቷ የተተገበረው የፌደራሊዝም ሥርዓት ፍሬ ነው ብለው ያምናሉ። ጆን ማርካኪስ ራስን የማስተዳደር ጥያቄና ነፃነትን ከመፈለግ የሚመነጭ እንደሆነ ከሚያነሱት ሃሳብ ጋር ይዛመዳል።

“ኢህአዴግ ‘ትምክህተኞችና ጠባቦች’ እያለ በጠላትነት የሚፈርጃቸው ወገኖች ጊዜና ፋታ እየጠበቁ ጥያቄ ማንሳታቸውን አያቆሙም” ይላሉ። “ችግሩም ያለው ከጠያቂዎቹ አይደለም፤ ከመላሹ እንጂ” በማለት ጨምረው ይናገራሉ።

አቶ ሙላቱም ሆነ ጀኔራል አበበ እንደ መፍትሄ የሚጠቁሙትም ትልቅ ህዝባዊ ውይይትና መነጋገርን ነው።

“ኢህአዴግ የተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ መሆኑን አምኖ ካልተቀበለ አገሪቷን ትልቅ ዕድል ያስመልጣታልም” ይላሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ጥያቄ እየተነሳ ያለው ኢህኣዴግ በጠላትነት ከሚፈርጃቸው ወገኖች አይደለም። በተቃራኒው ከህዝብ እንጂ። እንደ ምሳሌም የሚያነሱት በአማራ ክልል ሲውለበለብ የተሰተዋለውን አርማ የሌለበት ሰንደቅ ዓላማ “ህዝቡ ነው ያውለበለበው” ይላሉ። በቅርቡም የኦነግን ሰንደቅ አላማ የሚያውለበልቡ የኢሬቻ በአል ታዳሚዎች በኦሮሚያ ክልል ተስተውለዋል።

“እነዚህ ሰንደቅ ዓላማዎች ምን ማለት ናቸው?” ሲሉ ጀኔራሉ ይጠይቃሉ።

“እኩልነትን ያመጣል ተብሎ የታመነበት አዲሱ ሰንደቅ ዓላማ ከ25 ዓመታት በኋላ ይሄን ያህል ተቃውሞ የሚገጥመው ከሆነ፤ አንድም ህዝቡ አልተቀበለውም ወይም የማስረዳት ችግር አለ ማለት ነው” ይላሉ።

ጥያቄው መነሳቱ ተገቢ መሆኑን አምነው።

“የኢህኣዴግ አመራር ጥያቄዎቹን ማፈን እንጂ መመለስ አልቻለም በተቃራኒው አስተዳደራዊና የኃይል እርምጃ መውሰድን መርጧል” ይላሉ።

በኦሮሚያ የነበረው ተቃውሞImage copyrightGETTY IMAGES

ቀይ መብራት

የቀድሞው የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው ቀውሱን ከዚህ በተለየ መንገድ ይረዱታል። አገሪቷ በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ሥር ባለችበት ሁኔታ እንዲህ ዓይነት ቀውስ ተከስቶ የጋራ ነገር እየጠፋ መሄዱ አደገኛነቱ ያመዝናል ይላሉ። “በዚህ ሥርዓት ስር የተለያዩ ፖሊሲ ያላቸው ፓርቲዎች በምርጫ አሸንፈው የተለያዩ ክልሎችን ቢያስተዳድሩ፤ ምን ይውጠን ነበር?” በማለት ስጋታቸውን ይገልፃሉ።

በፖለቲካ ቀውሱ ምክንያት ተቃውሞና አመፅ እየተቀጣጠለ አገሪቷ ወደባሰ ደረጃ እየሄደችም እነደሆነ አቶ ልደቱ ይጠቅሳሉ። ይሄንን ሃሳብ አቶ ሙላቱም የሚጋሩት ሲሆን ሥርዓቱ መውደቅ ብቻ ሳይሆን አገሪቷ ወደበለጠ ማጥ ውስጥ እየገባችም ነው ብለው ያምናሉ።

“ኢትዮጵያዊ ነኝ በሚል የሚታወቀው አማራ፤ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ደረጃ ብሄርተኝነቱ እየጎለበተ መምጣቱ፤ ሁሉም የጋራ አገርን እየዘነጋ ወደ እየራሱ ማየት መጀመሩ ትልቅ ምልክት ነው” ይላሉ አቶ ልደቱ።

አቶ ልደቱ ብሔርን መሰረት ያደረገው ፌደራሊዝም ችግሮቹን አባብሷቸዋል ብለው የሚያምኑ ሲሆን የመገንጠልም ጥያቄዎችም ተጧጡፈዋል ይላሉ።

የዚህ ሥርዓት ሌላኛው ፈተና የተለያዩ ብሔር ተወላጆች በተለያዩ ክልሎች ተንቀሳቅሰው የመስራት እክሎች እያጋጠማቸው እንዲሁም “ከክልላችን ውጡ” በሚሉ መፈክሮች ብዙዎች መፈናቀላቸው አገሪቷ የመበታተን ጥላ እንዳጠላባት ተንታኞች ይናገራሉ።

በተቃራኒው ጀኔራል አበበ ከዚህ በፊት በ1966 እና በ1983 መንግሥት ባልነበረበት ታሪካዊ ቅፅበቶች እንኳን አገሪቷ አለመበተኗንና አሁንም ህዝቡ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት እንዳለ ይናገራሉ።

“ሥርዓቱ ይሆናል እንጂ አገር አትበታተንም” ብለዋል።

መፍትሔው ምን ይሆን?

ለተነሱት ከፍተኛ ተቃውሞዎች መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ እንዲሁም ብዙዎችን በማሰር መልስ የሰጠ ቢሆንም፤ ይህ የኃይል እርምጃ ቀውሱን ከማብረድ ውጭ እንዳልፈታው ቢቢሲ ያነጋገራቸው እነዚህ ተንታኞች ይናገራሉ።

“እንደ ቀድሞዎቹ መንግሥታት ኢሕአዴግም ተመሳሳይ ቀውስ ገጥሞታል፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ከመመለስ ይልቅ እንደ ቀደሙት መንግሥታት ችግሮቹን ለመፍታት ሠራዊቱን ማሳተፍን መርጧል” በማለት ጆን ማርካኪስ ይናገራሉ።

አቶ ሙላቱ እንደ መፍትሄ የሚጠቁሙትም እውነተኛ ፌደራሊዝምን መፍጠር፣ ህዝቡ የፈለገውን እንዲመርጥ መፍቀድ፣ የመናገርና የመፃፍ ነፃነትን ማክበር፣ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት እንዲሁም የአንድ ፓርቲ የበላይነት የሚያበቃበትን ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

አቶ ልደቱ በበኩላቸው ስርዓቱ ራሱን መፈተሽ እንዳለበትና አሁንም አገራዊ ውይይት እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተዋል።

“መንግሥት ወዶና ፈቅዶ መዋቅራዊ ለውጥ ካላመጣ፤ በኃይል ተገዶ ለውጥ መምጣቱ አይቀርም” ብለዋል።


Source: BBC